በጋምቤላ ክልል የታፈኑትን ህጻናት ለማስመለስ በቂ ትኩረት አልተሰጠም ተባለ

ኢሳት (ሚያዚያ 2 ፥ 2009)

ከጋምቤላ ክልል በቅርቡ ታፍነው የተወሰዱት ህጻናትን ለማስመለስ መንግስት በቂ ትኩረት አልሰጠም ሲሉ በጋምቤላ ክልል ስላለው የሰብዓዊ መብት መከበር ዙሪያ የሚሰሩ አካላት ገለጹ።

የኢትዮጵያ መንግስት ታፍነው የተወሰዱ ከ40 በላይ ህጻናትን ለማስለቀቅ ቃል ቢገባም፣ እስካሁን ድረስ የተመለሱ አለመኖራቸውንና ጥቃቱ በነዋሪው ዘንድ ስጋትን ማሳደሩን የደቡብ ሱዳን የዜና አገልግሎት ነዋሪዎችንና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች አካላትን ዋቢ በማድረግ ሰኞ ዘግቧል።

ባለፈው ወር ከደቡብ ሱዳን ድንበርን አቋርጠው በጋምቤላ ክልል ጥቃቱን የፈጸሙ የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች በትንሹ 28 ሰዎችን ገድለው ከ40 የሚበልጡ ህጻናትን ደግሞ አፍነው መውሰዳቸው ይታወሳል።

ጥቃቱን ተከትሎ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ወታደሮችን ወደ አካባቢው አሰማርቶ ታፍነው የተወሰዱ ህጻናትን ለማስለቀቅ ጥረትን እንደሚያደርግ ሲገልፅ ቆይቷል።

ይሁንና አገዛዙ ህጻናቱን ለማስመለስ ዕርምጃ እንዲወስድ ሲያሳስብ ቢቆይም ታፍነው የተወሰዱ ህጻናትና በሺዎች የሚቆጠሩ የቤት እንስሳት ሳይመለሱ መቅረታቸውን ዱአች ማች የተባሉ የማህበረቡ ተወካይና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች መግለጻቸውን የዜና አገልግሎቱ በጉዳዩ ዙሪያ ባቀረበው ሪፖርት አመልክቷል።

ተመሳሳይ ጥቃት ከአንድ አመት በፊት ተወስዶ እንደነበር ያወሱት ማች፣ መንግስት ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት ከደቡብ ሱዳን መንግስት ጋር የጋራ መፍትሄን እንዲያፈላልግ ጠይቀዋል።

ከአንድ አመት በፊት የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች በጋምቤላ ክልል በፈጸሙት ተመሳሳይ ጥቃት ከ100 የሚፈልጡ ሰዎች ተገድለው ሌሎች ከ100 የሚበልጡት ደግሞ ታፍነው መወሰዳቸው ይታወሳል።

በወቅቱ መንግስት በደቡብ ሱዳን መንግስት በኩል ድርድርን በማካሄድ አብዛኞቹ ታፍነው የተወሰዱት ህጻናት እንዲለቀቁ አድርጓል።

ጠቅላይ ሚኒስቴር ሃይለማሪያም ደሳለኝ ድርድርን ጭምር እንደአማራጭ በመውሰድ ታፍነው የተወሰዱት ህጻናት እንዲለቀቁ ማድረግ ይኖርበታል ሲሉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ግለሰቡ አክለው ተናግረዋል።

ባለፈው ወር ወደ ጋምቤላ ክልል ዘልቀው የገቡት የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች ቁጥራቸው ወደ 1ሺ አካባቢ እንደሚደርስና በጎግና ጆትር ተብለው በሚጠሩ ስፍራዎች (መንደሮች) በትንሹ 28 ነዋሪዎችን እንደገደሉ ኢንተርናሽናል ትሪቢዩን ጋዜጣ ዘግቧል።

በጋምቤላ ክልል ከአመት በፊት ተመሳሳይ ጥቃት ቢፈጸምም መንግስት ለጉዳዩ በቂ ትኩረት ሳይሰጥ መቆየቱን የጥቃቱ ሰለባ ተወካዮች ይገልጻሉ። የመንግስት ቃል አቀባይ የሆኑት ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ታግተው የተወሰዱ ህጻናትን ለማስለቀቅ ወታደሮችን ወደ አካባቢው እንዳሰማራ ለጋዜጠኞች መግለጻቸው የሚታወስ ነው።

ይሁንና የመከላከያ ሰራዊቱ አባላት የወሰዱት ዕርምጃ ይኑር አይኑር እስካሁን ድረስ የታወቀ ነገር የሌለ ሲሆን፣ ኢትዮጵያንና ደቡብ ሱዳን አንደኛው የሌላኛውን ሃገር ተቃዋሚ ላለመደገፍ ስምምነት መፈራረማቸው አይዘነጋም።