በጋምቤላ ክልል በሰፋፊ የእርሻ ልማት ለመሰማራት የሚፈልጉ ባለሃብቶች በባንክ የተቀመጠ 7.5 ሚሊዮን ብር ማሳየት እንደሚጠበቅባቸው ተገለጸ

ኢሳት (የካቲት 22 ፥ 2009)

በጋምቤላ ክልል ለሰፋፊ የእርሻ ልማት ስራ ሲሰጥ በቆየው ብድር በቢሊዮን ብር የሚቆጠር ኪሳራ የደረሰበት የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በዘርፉ መሰማራት የሚፈልጉ ባለሃብቶች በትንሹ 7.5 ሚሊዮን ብር ማሳየት እንደሚጠበቅባቸው አዲስ መመሪያን ተግባራዊ አደረገ።

ባንኩ ባለፉት ጥቂት አመታት በጋምቤላ ክልል ሲሰጥ በቆየው ብድር በርካታ ባለሃብቶች በተመሳሳይ መሬት ላይ ተደራራቢ ብድርን በመውሰድ ለብድር የተሰጠ ከሶስት ቢሊዮን ብር በላይ የገባበት ሳይታወቅ መቅረቱ ይፋ መደረጉ ይታወሳል።

የደረሰበትን ይህንኑ ከፍተኛ ኪሳራ ተከትሎ ከአንድ አመት በላይ ብድር መስጠት አቁሞ የነበረው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ከአሁን በኋላ በሰፋፊ የእርሻ ልማት ስራ መሰማራት የሚፈልግ አንድ ባለሃብት 7.5 ሚሊዮን ብር ሊኖረው እንደሚገባ ባወጣው መመሪያ አስፍሯል።

ባንኩ የደረሰበትን ኪሳራ ለማጥናት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት የተቋቋመ አንድ ብሄራዊ ቡድን ከ45ሺ ሄክታር መሬት በላይ በጋምቤላ ክልል ብቻ ተደራርቦ ለባለሃብቶች እንደተሰጠና ለደረሰው ኪሳራ ምክንያት መሆኑ በቅርቡ ይፋ አድርጓል።

በርካታ ባለሃብቶች ከባንኩ የወሰዱትን ብድር ይዘው የገቡበት ያልታወቀ ሲሆን፣ ቁጥራቸው ያልተገለጸ የህንድ ባለብሃብቶችም ብድራቸውን ሳያወራርዱ ከሃገር መኮብለላቸው ሲገለጽ ቆይቋል።

ባለፈው ወር ብድር የመስጠት ስራውን በአዲስ መልክ የጀመረው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ከዚሁ በኋላ ተመሳሳይ ችግር እንዳይገጥመው ያስችላል ያለውን ይህንኑ አዲስ መመሪያ ተግባራዊ እንዳደረገ ለሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን አስታውቋል።

7.5 ሚሊዮን ብር ማሳየት ይጠበቅባቸዋል የተባሉ ባለሃብቶች ይህንኑ ካፒታል ለአንድ አመት ማንቀሳቀሳቸው በባንኩ መረጋገጥ እንዳለበትም በአዲሱ መመሪያ ሰፍሯል።

የውጭ ባለሃብቶችን በተመለከተ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ብድርን ለማግኘት ከመጡበት ሃገር የብድር ታሪካቸው የሚያሳይ ማስረጃ ማቅረብ እንደሚኖርባቸው መስፈርትን ያስቀመጠ ሲሆን፣ የዝናብ እጦት በተደጋጋሚ በሚታይባቸው የሃገሪቱ አካባቢዎች ብድርን እንደሚሰጥም አክሎ ገልጿል።

በሰፋፊ የእርሻ ስራ ላይ የሚሰማሩ ባለሃብቶች ብድር በሚወስዱበት መሬት አቅራቢያ የመንገድ መሰረተ ልማትን ማካሄድ እንዳለባቸውም የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በአዲሱ መመሪያ ደንግጓል።

ይሁንና ከዚህ በፊት በኢንቨስትመንት ስራ ላይ የተሰማሩ ባለሃብቶች መንግስት የሚያቀርባቸው መሬቶች የመሰረተ-ልማት ያልተሟሉባቸው ናቸው በማለት ቅሬታን ሲያቀቡ ቆይተዋል። አዲሱን መመሪያ ይቀበሉ አይቀበሉት የታወቀ ነገር የለም። የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የደረሰበትን ኪሳራ ተከትሎ የጋምቤላ ክልል ሃላፊዎች ከስራቸው እንዲሰናበቱ የተደረገ ሲሆን ምክንያቱ ባይገለጽም የባንኩ ፕሬዚደንት ከሃላፊነታቸው እንዲነሱ መደረጉ ይታወሳል።

በአሁኑ ወቅት 260 ባለሃብቶች ከባንኩ ብድርን ለማግኘት ጥያቄን አቅርበው እንደሚገኙም ለመረዳት ተችሏል።