ኢሳት (ሚያዚያ 20 ፥ 2009)
በጋምቤላ ክልል በእርሻ ልማት ላይ ተሰማርተው የሚገኙ ከ260 በላይ ባለሃብቶች የክልሉ መንግስት ፈቃዳችንን ከስምምነት ውጭ ሰርዞብናል ሲሉ ቅሬታን አቀረቡ።
ባለሃብቶቹ በክልሉ በአንድ መሬት ላይ ተደራርቦ የተሰጠን የብድር አሰራር ተከትሎ ጉዳዩ እስኪጣራ ድረስ ስራችሁን ለጊዜው አቋርጡ ተብለው ከአንድ አመት በላይ መቆየታቸውን አስታውቀዋል።
ይሁንና፣ በመንግስት የተካሄደው ጥናት ከተጠናቀቀ በኋላ ወደ ቀድሞ ስራቸው እንመልሳለን ብለው ቢጠብቁም የጋምቤላ ክልል መንግስት የ269ኙን ባለሃብቶች ውል እንዲቋረጥ ማድረጉን የጋምቤላ ባለሃብቶች ማህበር ቅሬታውን አቅርቧል።
ቅሬታ አቅራቢዎቹ የተሰጣቸው የእፎይታ ጊዜ ሳያልቅ ውል እንዲቋረጥ መደረጉ ህግን ያላከበረ ነው ሲሉ የማህበሩ አመራሮችና ባለሃብቶቹ ለሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን አስረድተዋል።
ባለሃብቶቹ ገንዘባቸውን በባንክ አስይዘውና ተጨማሪ የብድር ጥያቄን አቅርበው ከሁለት አመት በላይ ሲጠባበቁ መቆየታቸውን አውስተው ጉዳዩን የሚመለከተው አካል ህጋዊ ምላሽ እንዲሰጥበት ጠይቀዋል። የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ባንክ በአንድ መሬት ላይ ተደራራቢ ብድር ሲሰጥ መቆየቱ በቢሊዮን ብር የሚቆጠር ኪሳራ እንዲደርስብት ምክንያት መሆኑ ሲገለጽ ቆይቷል።
ቢ ኤች ኦ (B.H.O) የተሰኘ የህንድ ኩባንያ በክልሉ ኢታንግ አካባቢ 27ሺ ሄክታር መሬት ተቀብሎ ስራ ከጀመረ በኋላ ከልማት ባንክ የወሰደውን ብድር ሳይመለስ ከሃገር መኮብለሉ ታውቋል።
በኩባንያው መሬት ላይ 22 ባለሃብቶች ተደራራቢ ይዞታ ፈቃድ ተሰጥቷቸው የነበረ ሲሆን፣ ባንኩ የደረሰበትን ኪሳራ ካጣራ በኋላ ባለሃብቶቹ ስራ እንዲያቆሙ ትዕዛዝ ሰጥቶ እንደነበር ቅሬታ አቅራቢዎቹ ባለሃብቶች አስረድተዋል። እስከ 450 ሄክታር መሬት ያለማና የብድር ድርሻውን 10 ሚሊዮን ብር ያስያዘ የባለሃብቶች ባለሃብት ውሉ እንዲቋረጥበት ከተዳረጉት ባለሃብቶች መካከል እንደሚገኙ የማህበሩ አመራሮች አስታውቀዋል።
ለልማት ባንክ ማስያዝ የሚጠበቅባቸውን በሚሊዮን የሚቆጠር ብር አስይዘው ተጨማሪ ብድርን ከአመት በፊት የሚጠባበቁ 25 ባለሃብቶችም የችግሩ ተጎጂ መሆናቸውን የጋምቤላ ባለሃብቶች ማህበር አክሎ ገልጿል።
የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ጋት ሉዋክ በበኩላቸው ክልሉ በፌዴራል መንግስት እጅ የነበረውን መሬት እንዲያስተዳድር ከተወሰነ በኋላ ጥናቱን ተመርኩዞ እየወሰደው ያለው ዕርምጃ ቅሬታ ማስነሳቱን ለመንግስት መገናኛ ብዙሃን ተናግረዋል።
በክልሉ ውሳኔ ቅሬታ ያደረባቸው ባለሃብቶች በመንግስት የተካሄደው ጥናት በድጋሚ እንዲታይላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ጥያቄ ማቅረባቸውም ታውቋል።
ጽ/ቤቱም የባለሃብቶቹ ጉዳይ በድጋሚ እንዲታይ መወሰኑንም ለመረዳት ተችሏል።
የብሄራዊ ባንክ በቅርቡ ባወጣው አዲስ መመሪያ በንግድ ባንክ በኩል ለልማት ፕሮጄክቶች ሲሰጥ የነበረው ብድር ቀርቶ የብድር ጥያቄ በኢትዮጵያ ልማት ባንክ በኩል እንዲስተናግድ ማድረጉ ይታወሳል። ይሁንና እርምጃው በባለሃብቶች ዘንድ ድንጋጤ ማሳደሩ ተሰምቷል።