በጋምቤላ በደረሰው ጭፍጨፋ የሞቱት ሰዎች ቁጥር በአስደንጋጭ ሁኔታ እየጨመረ ሲሆን መከላከያም እየየተቸ ነው

ሚያዚያ ፲(አሥር) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ባለፈው አርብ ከደቡብ ሱዳን የተነሱ ታጣቂዎች ከ35 እስከ 40 ኪሜ ወደ ኢትዮጵያ ድንበር ዘልቀው በመግባት በላሬ፣ ጃካዋ ወረዳዎች አካባቢ በሚኖሩ የኑዌር ተወላጅ ኢትዮጵያውያን ላይ አሰቃቂ የሚባል ግድያ በመፈጸም እስካሁን ባለው ቆጠራ 208 ሰዎች የተገደሉ፣ሲሆን ከእነዚህ መካከል 50 የሚሆኑት ህጻናት ናቸው፡፡ የኢሳት የጋምቤላ ታማኝ ምንጮች እንደገለጹት አስከሬን የመሰብሰቡ ስራ በተለያዩ ወረዳዎች እየተካደ ሲሆን፣ የሙዋቾች ቁጥር ከተጠቀሰው አሀዝ ሊልቅ ይችላል፡፡ እነዚሁ በደንብ የታጠቁና ከባድ መሳሪያ የያዙ ወታደሮች፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ህጻናትንና ሴቶችንም አፍነው ወስደዋቸዋል፡፡
ታጣቂዎቹ በማግስቱ ቅዳሜ ፉኝዶ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ዘልቀው በመግባት 10 የአኝዋክ ተወላጅ ኢትዮጵያውያንን በተጨማሪ ገድለው መውጣታቸውንም ምንጮች ጠቅሰዋል፡፡
ጥቃቱ በተፈጸመበት አካባቢ ምንም አይነት የመከላከያ ሰራዊት እንዳልነበረ የሚናገሩት ምንጮች፣ ጥቃቱ ከተፈጸመ በሁዋላ፣ የእርዳታ ድርጅቶች ሰራተኞች ወደ መከላከያ ሰራዊት ካፕም በመሄድ፣ እርምጃ እንዲወሰድ መጠየቃቸውን፣ ይህን ተከትሎም፣ ከአዲስ አበባ ትእዛዝ እስከሚጣ፣ ረጅም ሰአት መውሰዱን ተናረዋል፡፡
ትእዛዝ ከመጣ በሁዋላ ደግሞ የኢትዮጵያ ወታደሮች ወደ ድንበር የሚወስዳቸው መኪኖች በመታጣታቸው፣ ከተለያዩ መንግስታዊ እና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች መኪና ጠይቀው፣ መሄዳቸውን ተናግረዋል፡፡ መከላከያ ሰራዊቱ የአጸፋ እርምጃ ወስዶ 61 የሚሆኑ የሙሪሌ ጎሳ ታጣቂዎች መገደላቸውን በመገናኛ ብዙሃን ቢገለጽም፣ የአለማቀፍ የእርዳታ ድርጅቶች ሰራተኞች ግን ከተቃራኒው ወገን ምንም የተገደለ ሰው አለማየታቸውን ተናግረዋል፡፡ መንግስት ህዝቡን ለማረጋጋት የተናገረው ሊሆን ይችላል እንጅ በኢትዮጵያ ክልል ውስጥ የተፈጸመ የመልሶ ማጥቃት እርምጃ ስለመኖሩ የሚያረጋግጥ ማስረጃ የለም ሲሉ ይገልጻሉ፡፡ እነዚህ ምንጮች እንደሚሉት ሰራዊቱ መኪና አፈላልጎ ወደ ድንበር የተንቀሳቀሰው ጥቃቱ ከተፈጸመ ከብዙ ሰአታት በሁዋላ በመሆኑ፣ ታጣቂዎችን የማግኘት እድሉ አነስተኛ ነው፡፡
በሌላ በኩል አንዳንድ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ፣ በቂ የሆነ ሎጂስቲክስ ቢኖር እና ፈጣን ትእዛዝ ቢሰጥ ኖሮ፣ ታጣቂዎችን በቀላሉ መደምሰስ ይቻል ነበር ይላሉ፡፡ በአካባቢው የተሰማራው ሰራዊት፣ ከአዲስ አበባ አቅጣጫ ካልተሰጠው በስተቀር ምንም አይነት እርምጃ የማይወስደ በመሆኑ፣ ትእዛዝ ከተሰጠው በሁዋላም ቢሆን፣ የሎጂስቲክ አቅርቦት ስላልነበረው ፣ ጉዳቱ የከፋ ሆኖአል በማለት በአካባቢው የተሰማራውን መከላከያ በቅርበት የሚያውቁት እነዚህ ወገኖች ቅሬታቸው ገልጸዋል፡፡
ጥቃቱ ለምን በኑዌሮች ላይ ብቻ አነጣጠረ፣አንዳች ፖለቲካዊ ፋይዳ ይኖረው ይሆን የተባሉት ሰራተኞች፣ ግጭቱ የጎሳ ግጭት አለመሆኑ፣ ጥቃቱን የፈጸሙትም በደንብ የተደራጁ ሃይሎች በመሆኑ፣ ተራ ዝርፊያ ነው ብሎ ለመቀበል እንደሚያስቸግር ተናግረዋል፡፡
መድረክና ሰማያዊ ፓርቲ በደረሰው ጉዳት ሀዘናቸውን ገልጻዋል፡፡ፓርቲዎቹ በጋራ ባወጡት መግለጫ ዜጎቻችን ለዚህ ያህል ትልቅ ጥቃት የተዳረጉት ፣ ቀደም ሲልም ጥቃት ሲፈጸሚባቸው እንደነበረ እየታወቀ ፣ የኢህአዴግ መንግሥት እራሳቸውን የሚከላከሉበትን ትጥቅ በማስፈታቱ የመከላከያ መሣሪያ እንዳይኖራቸው በመደረጉና ባዶ እጃቸውን በቀሩበት ሁኔታ ለደህንነታቸው ተገቢው ጥበቃ ስላልተደረገላቸው መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ከዚህም ሌላ ቀደም ባሉት መንግሥታት በየጠረፉ አከባቢዎች ይመደብ የነበረው ጠረፍ ጠባቂ ኃይል እንዳይኖር በመደረጉ የውጭ ሀገር ታጣቂዎች እንደፈለጉ ድንበርጥሰው የሚገቡበትና ወገኖቻችን ላይ ጥቃት የሚያደርሱበት ሁኔታ የተፈጠረ መሆኑንም ለመረዳት ችለናል ካሉ በሁዋላ፣
በአጥቂዎቹ ታፍነው የተወሰዱት ሕፃናት በሰላም ወደ ቤተሰቦቻቸው እንዲመለሱ መንግሥትና የዓለም ማሕበረሰብከፍተኛ ትኩረት ሰጥተው ተገቢውን ጥረት ሁሉ እንዲያደርጉ ፣ ለወደፊቱ በጋምቤላም ሆነ በሌሎች ክልሎች በጠረፍ አከባቢዎች በሚገኙ ዜጎቻችን ላይ ተመሳሳይጥቃቶች እንዳይፈጸሙ ሕዝቡ ራሱን መከላከል የሚችልበትና ተገቢውን የደህንነት ጥበቃ የሚያገኝበት ሁኔታበአስቸኳይ በመንግሥት በኩል እንዲመቻች አጥብቀን እንጠይቃለን ብለዋል፡፡
የአ/አ ዘጋቢያችን ያነጋገራቸው የአዲስአበባ ነዋሪዎች ይህ ሁሉ ሲሆን በአገሩ መንግስት የለም ወይ ሲሉ በቁጭት ጠይቀዋል።
አንድ በሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት መምህር የሆኑ ጎልማሳ በሰጡት አስተያየት በአጼውም ሆነ በደርግ ዘመነ መንግስት እንዲህአይነት ከባድ ጥቃት አይተውና ሰምተው እንደማያውቁ ገልፀው የመከላከያ ሰራዊት አገር ሰላም በሆነበት ወቅት ድንበርመጠበቅ ዋና ተግባሩ መሆኑ እንደሚያውቁ ጠቅሰው ይሄ ሁሉ ጥቃት የተፈጸመው ይህ ሰራዊት የት ሄዶ ነው ሲሉ በአዘኔታ ጠይቀዋል።
መንግስት ባለበት ሀገር ከውጭ ሀገር የመጣ ታጣቂ በመቶዎች ወገናችንን ሲገድል ከመስማት የበለጠ አሳዛኝ ነገርየለም ያሉት ሌላኛው አስተያየት ሰጪ መንግስት ጅብ ከሄደ ውሻ ጮኸ አይነት ቀረርቶውን ትቶ በእንዝላልነት ለደረሰው
ጥቃት ተጠያቂ የመከላከያ ባለስልጣናትን ለፍርድ ሊያቀርብ ይገባል ብሎአል።
በአዲስአበባ ከተማ ጥቃቱ ከተሰማ በሀላ የህዝብ ቁጣና ቁጭት የተቀጣጠለ ሲሆን፣በየመ/ቤቱና በየአካባቢው ህ/ሰቡበጉዳዩ ላይ እየተወያየ ይገኛል :: ብዙ ወገኖችም መንግስት ወቅታዊ የወገኖቻችንን ጥቃት መመከት ባለመቻሉ እያወገዙት ይገኛሉ።
ከ300 ሺ ህዝብ በላይ የሚኖርባት ጋምቤላ ኑዌር፣ አኙዋክ፣ ማጃንግ፣ ኮሞ እና ኦፓ የተባሉ አምስት ነባር ብሄረሰቦች አቅፋ ይዛለች፡፡