በጋምቤላ ማንነታቸው ያልታወቁ ታጣቂዎች ጉዳት በማድረስ ላይ መሆናቸውን ተከትሎ በርካታ ሰዎች ክልሉን እየለቀቁ ነው
ከትናንት በስቲያ በጋምቤላ ማንነታቸው ያልታወቁ ሰዎች የፈጸሙትን ጥቃት ተከትሎ፣ የመሀል አገር ሰዎች ወይም በተለምዶ ደገኞች እየተባሉ የሚጠሩ ነዋሪዎች ተመሳሳይ ጥቃት ይፈጸም ይሆናል በሚል ስጋት አካባቢውን በአለው የትራንስፖርት አማራጭ ሁሉ እየለቀቁ ነው። በርካታ ነዋሪዎች ወደ አጎራባች ክልሎች በመኪና መጓዛቸውን በአይኑ መመልከቱን ወኪላችን ገልጦአል።
በትናንትናው እለት በርካታ የፌደራልና የመከላከያ ሰራዊት አባላት በጋምቤላ በብዛት መጥተው የሰፈሩ ሲሆን፣ በየትኛውም የከተማው መውጫ እና መግቢያ በሮች ከፍተኛ ፍተሻዎችን እያደረጉ ነው። መንገደኞች ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ በፌደራል ፖሊስ መኪኖች እየታጀቡ ሲጓዙ አርፍደዋል።
በትናንትናው እለት ከቀኑ 11 ሰአት ጀምሮ በከተማዋ የአኝዋክና የኑዌር ተወላጆች በመንገድ ላይ ሲጓዙ አለመመልከቱን የገለጠው ዘጋቢአችን፣ ድርጊቱ ተወላጆቹ በመንግስት ላይ ያላቸውን ተቃውሞ ለመግለጥ ይመስላል ብሎአል። የአካባቢው ተወላጆች ቤታቸውን ዘግተው መቀመጥ መንግስትን ጋራ ያጋባ ጉዳይ ሆኗል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በታጣቂዎች ወዲያውኑ የተገደሉት እና በሁዋላ ላይ ሆስፒታል ውስጥ የሞቱት 2 ተማሪዎች በድምሩ 19 ተማሪዎች ወደ መጡበት ወረዳ ትናንት ከሰአት በሁዋላ ሄደዋል። አስከሬኑን በጫነው መኪና ላይ ” መንግስት አፋጣኝ መልስ ይሰጠን” የሚል ባነር ተለጥፎ መመልከቱን ዘጋቢያችን ገልጧል።
ኢሳት በትናንት ዘገባው 17 ተማሪዎች ህይወታቸው ማለፉን፣ 8 ተማሪዎች በጽኑ ቆስለው መትረፋቸውን መዘገቡ ይታወሳል። የመለስ መንግስት ጥቃቱን የፈጸሙት ጸረ ሰላም ሀይሎች ናቸው ቢልም፣ ጸረ ሰላም የተባሉትን ሐይሎች ግን በስም አልጠቀሰም። የክልሉ ፕሬዚዳንት የሆኑት አቶ ኦቦንግ ኦሞድ ግን ጥቃቱን የፈጸሙት በ1996 አኩርፈው የወጡ ሽፍቶች ናቸው ይላሉ።
ጥቃቱን የሚፈጽሙትን ወገኖች አላማ እና ፍላጎት የኢሳት ወኪል ከተወላጆቹ የኑዌርና የአኝዋክ ነዋሪዎች ጋር በመነጋገር ለማጣራት ተደጋጋሚ ጥረት ቢያድርግም፣ በሚያስግርም ሁኔታ ተወላጆቹ ስለጥቃቶቹ አንድም ቃል አይተነፍሱም፣ ስለጉዳዩም ሲያወሩ አይሰሙም ብሎአል። መንግስት የክልሉን መሬት በርካሽ ወጋ መቸብቸቡና ነዋሪውን ማፈናቀሉ በክልሉ ለተፈጠረው ውጥረት መንስኤ ሳይሆን አይቀርም። የጋምቤላ ተወላጆች የመንግስት የግዳጅ ሰፈራና የመሬት ሽያጭ አጥብቀው እንደሚቃወሙ የአለማቀፍ ተቋማት የሚያወጡት ዘገባ ትክክል መሆኑን ያሰባሰበውን መረጃ ዋቢ በማድረግ ይገልጣል።
___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________
ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.
ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide