በጋምቢያ ፕሬዚደንታዊ ምርጫ የተሸነፉት ያህያ ጃምህ የምርጫውን ውጤት አልቀበልም ማለታቸውን ተከትሎ በአገሪቱ ውጥረት መንገሱ ተገለጸ

ኢሳት (ታህሳስ 3 ፥ 2009)

የጋምቢያው ፕሬዚዳንት የምርጫ ሽንፈታቸውን የተቀበሉበት ብሄራዊ ምርጫ በድጋሚ እንዲካሄድ ያቀረቡ አዲስ ሃሳብ በሃገሪቱ ውጥረት ማንገሱ ተገለጸ።

የአለም አቀፉ ማህበረሰብ የጋምቢያው ፕሬዚደንት ያህያ ጃምህ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግርን እንዲያደርጉ ቢያሳስቡም በ24 ሰዓት ውስጥ ቃላቸውን የቀየሩት ፕሬዚደንቱ የምርጫው ግድፈት ነበረው በማለት ድጋሚ ምርጫ እንዲካሄድ ጠይቀዋል።

ይሁንና በ22 አመት የስልጣን ዘመናቸው የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን እንዲፈጸሙ የሚነገርላቸው ፕሬዚደንት ያህያ ከእሁድ ጀምሮ በመዲናይቱ ባንጁል ወታደሮቻቸውን እንዳሰማሩ አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል። Yahya Jammeh

ፕሬዚደንታዊ ምርጫውን ያሸነፉት አዳማ ባሮው በበኩላቸው ለደህንነታቸው ስጋት እንዳደረባቸውና ተሸናፊው ፕሬዚደንት  የያዙትን አቋም የዴሞክራሲ ግንባታን ከገደል የከተተ ተግባር እንደሆነ አስታውቀዋል።

የፕሬዚደንቱ ታማኝ ናቸው የተባሉ ወታደሮች በመዲናይቱ ባንጁል የ24 ሰዓት ቁጥጥርን እያደረጉ ሲሆን፣ ፕሬዚደንቱ ያህያ ምርጫው በድጋሚ እንዲካሄድ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ጥያቄን እንደሚያቀርቡ እሁድ ይፋ አድርገዋል።

ይሁንና የጸጥታው ምክር ቤት እና የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ለ22 አመት በስልጣን የቆዩት ፕሬዚደንቱ ቃላቸውን በማክበር በትንሿ ምዕራባዊ ሃገር ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር እንዲያደርጉ ጥሪን አቅርበዋል።

በአለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ዘንድ መነጋገሪያ ሆነው የሚገኙት የጋምቢያው ፕሬዚደንት ከ22 አመት በፊት በመፈንቅለ-መንግስት ዕርምጃ ለስልጣን መብቃታቸው ይታወሳል።

ይሁንና ፕሬዚደንቱ በስልጣን በቆዩበት ዘመን ተቀናቃኞቻቸውን እንዲሁም በጋዜጠኞች ላይ የከፋ ዕርምጃን ሲወስዱ መቆየታቸውን የተለያዩ የሃገሪቱ አለም አቀፍ አካላት ይገልጻሉ።

በቱሪስት መስብህነቷ የምትታወቀውን እና ሁለት ሚሊዮን አካባቢ ብቻ ህዝብ ያላትን ሃገር በመምራት ላይ ያሉት ፕሬዚደንት ያህያ ለፍርድ ቤት አቀርባለው ያሉት አቤቱታ መቼ እንደሚቅርብ የታወቅ ነገር የለም።

የተለያዩ ሃገራትና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት በበኩላቸው ፕሬዚደንቱ እንደልባቸው የሚያዙት የሃገሪቱ የፍትህ አካል ጥያቄውን በመቀበል በጋምቢያ ዳግም ምርጫ እንዲካሄድ ውሳኔን ሲሰጥ ይችላል ሲሉ ስጋታቸውን እየገለጹ ይገኛል።