በጊምቢ እስር ቤት ውስጥ ምንነቱ ያልታወቀ በሽታ ተከስቶ አንድ እስረኛ ሲሞት 60 ዎቹ በጸና መታመማቸው ተገለጸ

ታኀሳስ (ሁለት) ቀን ፳፻፯ / ኢሳት ዜና :-የምስራቅ አፍሪካ የሰብአዊ መብት ሊግ የተባለው ተቋም ለኢሳት በላከው መግለጫ በምእራብ ወለጋ በጊምቢ እስር ቤት በተከሰተው ምንነቱ ያልታወቀ በሽታ አቶ ያቆም ኒጋሩ የተባሉ የፖለቲካ እስረኛ አርፈዋል። ሌሎች በበሽታው የተያዙት 60 ዎቹ እስረኞችም ተመሳሳይ እጣ ሊገጥማቸው እንደሚችል ስጋቱን ገልጿል።

ሟቹ አቶ ያእቆብ ባለፈው ሚያዚያና ግንቦት ወር በኦሮምያ ተከስቶ ከነበረው ተቃውሞ ጋር በተያያዘ በሽብርተኝነት ከተከሰሱት  224 የኦሮሞ ተወላጆች መካከል መሆናቸውን ሊጉ ገልጿል። የፖለቲካ እስረኞቹ በቂ ህክምና እንዳያገኙ በማድረግ እየተቀጡ መሆኑንም ሊጉ አክሎ ገልጿል።

በማእከላዊ እስር ቤት ከታሰሩት መካከል የሃሮማያ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች የሆኑት አበበ ኡርጌሳና  መገርሳ ወርቁ፣ የአዳማ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ሆኑት አዱኛ ኬሶና ቢሉሱማ ደመና ፣ የጅማ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች የሆኑት ተሻለ በቀለና ሊጂሳ አለማየሁ በእስር ቤት ውስጥ ከፍተኛ ማሰቃየት ወይም ቶርቸር ተፈጽሞባቸዋል።

ሊጉ 29 የኦሮሞ ተማሪዎች በሚያዚያውና በግንቦቱ ተቃውሞ ተሳትፋችሁዋል በሚል የመመረቂያ ሰርተፊኬት እንደተከለከሉ አክሎ ገልጿል።