በጉጂ ዞን ግጭት ተቀሰቀሰ

(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 5/2010)  በኦሮሚያ ክልል በጉጂ ዞን ሀገረማርያም ከተማ ብሄር ተኮር ግጭት ተቀሰቀሰ።

ፋይል

የጌዲዮ ተወላጆች ከከተማችን ይውጡልን የሚሉ ግለሰቦች ቀሰቀሱት በተባለው በዚሁ ግጭት በርካታ ሰዎች መገደላቸው ተነግሯል ።

ወደሀገረማርያም የስልክ አገልግሎትም መቋረጡ ተሰምቷል።

ከዲላ በኋላ ያለውም መንገድ ተዘግቷል።

ከ15ሺ በላይ ሰዎች መፈናቀላቸውንም የአካባቢው ምንጮች ገልጸዋል።

እያበቃ ባለው ሳምንት መጀመሪያ አንስቶ በጉጂ ዞንና በጌዲዮ ዞን ድንበር አካባቢ በጉጂና በጌዲዮ ብሔረሰቦች መካከል ግጭት መቀስቀሱን ነው ለኢሳት የደረሰው መረጃ የሚያመለክተው።

ባለፉትቀናት  በምዕራብ ጉጂ ዞን ስር በምትገኘው ቀርጫ ወረዳ የጌዲዮ ብሔረሰብ አባላት ተገደው ከኖሩበት ቀዬ ንብረታቸውን ጥለው እንዲወጡ መደረጋቸውን የአከባቢው ነዋሪዎች ይናገራሉ።

ሁኔታው ያዝ ለቀቅ እያደረገው ሁለት ቀናትን ከቆየ በኋላ ከትላንት ምሽት አንስቶ ወደለየለት ግጭት መለወጡን ለኢሳት በደረሰው መረጃ ላይ ተመልክቷል።

በተለይም ሰሬ በሚባለው አከባቢ ጠንከር ያለ ግጭት መከሰቱን ለማወቅ ተችሏል።  ከሁለቱም ወገኖች በርካታ ሰዎች መገደላቸው እየተነገረ ነው።

መሳርያ የታጠቁ በርካታ ቁጥር ያላቸው የጉጂ ብሄር ተወላጆች ድጋፍ ለማድረግ ግጭቱ ወደተከሰተበት ስፍራ በማምራት ላይ መሆናቸውንም የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

ይህ ዜና በሚጥናቀርበት ጊዜ ግጭቱ መቀጠሉን የሚገልጹት የአከባቢው ነዋሪዎች ከ15ሺህ በላይ ሰዎች ተፈናቅለው ወደ አገኙት አቅጣጫ በመሸስ ላይ መሆናቸው ታውቋል።

በግጭቱ በርካታ ሰዎች መገደላቸው የተገለጸ ሲሆን ቁጥራቸውን ለማወቅ ያደርግነው ጥረት ለጊዜው አልተሳካም።

ከዲላ ጀምሮ ወደ ሞያሌ የሚወስደው ዋናው መንገድ የተዘጋ ሲሆን በአከባቢው የስልክ አገልግሎት ሙሉ በሙሉ ተቋርጧል።

ዘግይቶ በደረሰን ዜናም የመከላከያ ሰራዊት በአከባቢው በመግባት ላይ ነው።

ብላቴ ከተሰኘው ወታደራዊ ካምፕ የተጓጓዙት የመከላከያ ሰራዊት አባላት ግጭቱ የተከሰተባቸውን አከባቢዎች ለመቆጣጠር ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ከሁለት ዓመት በፊት በጌዲዮ ዞን በተቀሰቀሰ ግጭት ከ30 በላይ ሰዎች መገደላቸውንና የአከባቢው ተወላጆች አይደላችሁም በሚል በተፈጸመ የንብረት ጥቃት በርካታ ሚሊዮን ብር የሚገመት ሀብት መውደሙ የሚታወስ ነው ነው።

በተያያዘ ዜና  በሞያሌ ዳግም ግጭት መቀስቀሱን ለኢሳት የደረሰው መረጃ ያመለክታል።

በሶማሌያ ገሪ በሚባል ጎሳና በቦረና ኦሮሞዎች መካከል የተጀመረው ግጭት በሰው ላይ ከፍተኛ የአካል ጉዳት ያደረሰ ሲሆን የሞት አደጋ ስለመከሰቱ የታወቀ ነገር የለም።

ዛሬ በሞያሌ ከተማ በመሳሪያ  ጨምሮ በድንጋይ እርስ በርስ ግጭት መካሄዱ ታውቋል። በዚህም ምክንያት ሱቆች ስራ አቁመዋል።  የንግድ እንቅስቃሴ ተገቷል።

መንገዶች ተዘግተዋል። በሞያሌ ዙሪያ ያሉ መንደሮች ጭምር በውጥረት ውስጥ መሆናቸውን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

የህወሀትት መከላከያ እና ልዩ ሃይል ወታደሮች በከተማው መውጫና መግቢያ ላይ በብዛት ሰፍረው እንደሚገኙም ተገልጿል።

የግጭቱ መንስዔ ባይታወቅም ለወራት የቀጠለውና በሶማሌና ኦሮሞ ተወላጆች መሃል የተካሄደው ግጭት አካል ሊሆን እንደሚችል የኢሳት የመረጃ ምንጮች ገልጸዋል።