ሐምሌ ፲፱ ( አሥራ ዘጠኝ ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ሃምሌ 16 ቀን 2009 ዓም ከቀንድ ከብቶች መዘረፍ ጋር በተያያዘ በጉጂ ኦሮሞዎችና በኮሬ ብሄረሰብ መካከል የተጀመረው ግጭት ተባብሶ ቀጥሎአል። ካለፉት 4 ቀናት ጀምሮ በመካሄድ ላይ ባለው ግጭት እስካሁን ከሁለቱም ወገን ከ13 በላይ ሰዎች ህይወታቸው ያለፈ መሆኑን እና ከ300 በላይ ቤቶች መቃጠላቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል። በተለይ ገልማ መታሪ በሚባለው አካባቢ ዛሬ ውጊያው መባባሱን ነዋሪዎች አክለው ገልጸዋል።
በግጭቱ የደቡብ ልዩ ሃይል ገብቶ ጥቃት መሰንዘሩን መዘገባችን ይታወሳል። የፌደራል ፖሊስ አባላት ወደ አካባቢው መንቀሳቀሳቸውም ተነግሯል። በዚሁ ግጭት የፖሊስ አባላት ሳይቆስሉ እንዳልቀረም የአካባቢው ነዋሪዎች ይናገራሉ።
ገዢው ፓርቲ ከዚህ ቀደም በኦሮሞና በሶማሌ፣ በአፋርና አማራ መካከል እንዳደረገው ሁሉ አሁንም ህዝቡ በአንድነት እንዳይተባበር ሆን ብሎ ያስነሳው ግጭት ነው በማለት የአካባቢው ነዋሪዎች ይናገራሉ። የሁለቱ አካባቢ ነዋሪዎች ለዘመናት አብረው የኖሩ መሆናቸውን የሚናገሩት ነዋሪዎች፣ የአሁኑ ጸብ በአካባቢው እየተነሳ ያለውን ተቃውሞ ህዝብን በመከፋፈል ለማዳከም የታለመ ነው ይላሉ።