በጉራጌ ዞን የተጀመረው አድማ ለ6ኛ ቀን ቀጥሎአል
(ኢሳት ዜና የካቲት 13 ቀን 2010 ዓ/ም) በወልቂጤ፣ በጉብሬ፣ በአገናና በሌሎችም አካባቢዎች የተጀመረው የስራ ማቆም አድማና ተቃውሞ ለስድሰተኛ ቀን መቀጠሉን ከስፍራው የደረሰን መረጃ ያመለክታል።
የስራ ማቆም አድማው ወደ አደባባይ ተቃውሞ ተሸጋግሮ የተወሰኑ ሰዎች በጸጥታ ሃይሎች መገደላቸው ይታወሳል። ተቃውሞው አድማሱን በማስፋት ወደ እዣ፣ ቺሃ፣ እምድብር፣ እነሞር እና ኢነር ወረዳ የጉመር ወረዳን መቀላቀላቸውን ወኪላችን ገልጿል። ታላላቅ የሚባሉት ገበያዎች ከእዣ ወረዳ አገና ገበያ፣ ከጉብሬ፣ ጉብሬ ገበያና በቸሃ ወረዳ የእምድብር ገበያዎች ባለፈው ሃሙስና አርብ ተበትነዋል።
እስካሁን ድረስ 16 የመንግስት ተሽከርካሪዎችን ጨምሮ የፖሊስ ጽ/ቤትና ሌሎችም በርካታ መስሪያ ቤቶች ተቃጥለዋል። የጉራጌ ዞን ብሄራዊ ንቅናቄ ሃላፊና የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ የአቶ ሙሃመድ ቤት እንዲሁም አንድ ግለሰብ እንዲገደል ትእዛዝ ሰጥቷል የተባለ ፖሊስ አዛዥ መኖሪያ ቤትም ተቃጥሏል።
ትናንት አድማው እንዲቆምና ድርጅቶች እንዲከፈቱ የሃይማኖት አባቶች ሽምግልና የጀመሩ ቢሆንም፣ ህዝቡ “ወደ ትግራይ የተወሰደው የሆስፒታል ፕሮጀክት እንዲመለስ፣ የታሰሩት በሙሉ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱ፣ የአጋዚ ሰራዊት ከአካባቢው እንዲወጡ” የሚል ቅድመ ሁኔታዎችን ያስቀመጠ ሲሆን፣ ይህ ካልሆነ ግን ተቃውሞአችንን አናቆምም፣ ድርጅቶቻችንንም አንከፍትም ማለቱን ወኪላችን ገልጿል።