በገጠር መንገዶች ላይ ሚታየው የጥራት ችግር አሁንም አለመፈታቱ ተነገረ፡፡

መስከረም ፲፱ (አስራ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የአማራ ገጠር መንገድ ስራ ባለስልጣን መስሪያ ቤት ባደረገው አመታዊ የሰራተኞች ስብሰባ ላይ ችግሩ አለመቀረፉን የገለጹት ባለሙያዎችና የድርጅቱ ሰራተኞች ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በተደጋጋሚ የሚያሳማው የጥራቱ ጉዳይ መሆኑን ተናገረዋል፡፡
ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ሁልጊዜ ሊያሻሽለው አልቻለም በማለት ባለሙያዎች ያቀረቡት የጥራት ጉዳይ መንገዶች ጥገና ተደርጎላቸው ከተሰሩ በኋላም ተገቢውን ጊዜ አገልግሎት ሳይሰጡ በመበላሸታቸው በወረዳና ዞን አካባቢ የሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎች በመቸገር ተደጋጋሚ አቤቱታ እንደሚያሰሙ ተናግረዋል፡፡
አብዛኛውን ጊዜ በሜዳማ ቦታዎች የሚሰሩ መንገዶች ዳርና ዳር ካለው የመሬት አቀማመጥ ወደ ስር በመግባት መገንባታቸው በላያቸው ላይ ውኃ እንዲፈስና ቶሎ አገልግሎታቸውን እንዲጨርሱ የሚያደርግ አሰራር መከተል የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የተለመደ ችግር እየሆነ መምጣቱን ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡
በክልሉ የገጠር መንገድ ባለስልጣን መስሪያ ቤት በተሰሩ መንገዶች ላይ የተነሱ ችግሮች በሙሉ ትክክል መሆናቸውን የተናገሩት ሌላው የመስሪያ ቤቱ ባለሙያ፣ በጥሬ ዕቃ አቅርቦት ላይ በሚያጋጥም ችግር ምክንያት በአካባቢው በሚገኝ ጥራቱን ባልጠበቀ ጥሬ ዕቃ መስራታቸው ለመንገዱ ጥራት መጓደል አንድ ምክንያት መሆኑን በተደጋጋሚ በአካል በመገኘት የታዘቡት መሆኑን ገልጸዋል። ይህን ችግር ከወረዳ እስከ ዋና ስራ አስኪያጅ ድረስ ጉዳዩ ለሚመለከታቸው አመራሮች ቢያቀርቡም ከመልካም ምላሽ ይልቅ ‹‹ ለምን ይሄን አነሳችሁ? ›› በማለት ችግር እንደተፈጠረባቸው ተናግረዋል፡፡