በገንዳሆ ከተማ በመከላከያ ሰራዊትና ጸረ-ሽምቅ በሚባሉት ልዩ ሀይሎች መካከል በተደረገው የተኩስ ልውጥጥ በርካታ ሰዎች ተገደሉ

ሰኔ ፳፮ (ሃያ ስድስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና :-በመተማ ወረዳ በገንዳሆ ከተማ ሰኔ 25፣ 2005 ዓም ከሌሊቱ 5 ሰአት ከ30 ላይ በመከላከያ ሰራዊት እና ጸረ-ሽምቅ እየተባሉ በሚጠሩ ሀይሎች መካከል በተካሄደው የተኩስ ልውውጥ ከ4 እስከ 7 የሚደርሱ  ታጣቂዎችና የመከላከያ ሰራዊት አባላት ሲገደሉ፣ 2 የወረዳው ባለስልጣናት ደግሞ ቆስለዋል።

በሰሜን ጎንደር ዞን በሚገኙ የተለያዩ ወረዳዎች ውስጥ የሚገኙ ጸረ-  ሽምቅ እየተባሉ የሚጠሩ ከ 150-200 የሚደርሱ የመንግስት ታጣቂዎች ለወታደራዊ እና ፖለቲካዊ ስልጠና በሚል በቀድሞ ስሟ ሽንዲ በአዲሱ ስሟ ገንዳሆ ከተማ ካለፈው ሳምንት ጀምሮ የተሰባሰቡ ሲሆን፣ ትናንት ምክንያቱ በውል ባልታወቀ ሁኔታ በአካባቢው ሰፍሮ ከሚገኘው የመከላከያ ሰራዊት ጋር ሌሊቱን ሙሉ ጎራ ለይተው ሲታኮሱ አድረዋል።

ለኢሳት የደረሰው መረጃ እንደሚያመለክተው ከመከላከያ 2 ከጸረ- ሽምቅ ሀይሎች ደግሞ 3 ሰዎች ሲገደሉ፣ አበበ የሚባል የወረዳው የጸጥታ ዘርፍ ሃላፊና ሌላ ባለስልጣን ቆስለዋል። ከሟቾች መካከል ወረቀት የሚባለው ሰው አስከሬኑ ወደ ሳንጃ  ተልኳል። የአካባቢው ነዋሪዎች እንደሚሉት የሟቾችን ቁጥር ከተጠቀሰውም አሀዝ ይልቃል።

የወረዳው የፖሊስ አዛዥ የሆኑት ኢንስፔክተር አስማማው ስብሰባ ላይ በመሆናቸው መረጃ ለመስጠት እንደማይችሉ ገልጸዋል። ምሽት ላይ በድጋሜ ስንደውልላቸው ስልካቸውን ለማንሳት ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።

በቅርቡ በመተማ ወረዳ ከመሬት ጋር በተያያዘ ከ50 እስከ 60 የሚጠጉ አርሶ አደሮች ጫካ መግባታቸው  ይታወቃል። የአካባቢው ነዋሪዎች ብሎክ የሚል ስያሜ የሰጡትን መሬት የማከፋፈል ስርአት፣  የመንግስት ታጣቂዎች ሳይቀሩ ሲቃወሙት ቆይተዋል።