በጅጅጋ የስራ ማቆም አድማ ተጀመረ

(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 19/2010) በሶማሌ ክልል ዋና ከተማ ጂጂጋ የስራ ማቆም አድማ ተጀመረ።

በከተማዋ የንግድም ሆነ የተሽከርካሪ እንቅስቃሴ ሙሉ በሙሉ መቆሙን ለኢሳት የደረሰው መረጃ ያመለክታል።

በተያያዘ ዜና በሽንሌ ከተማ ከፍተኛ ህዝባዊ ተቃውሞ ሲካሄድ ውሏል።

የአጋዚ ሰራዊት ከሶማሌ ክልል ልዩ ሃይል ጋር በመሆን በህዝቡ ላይ ርምጃ በመውሰድ ላይ መሆነ ተገለጿል።

የአጋዚ ወታደሮች ባርባራት በሚል የሚታወቁትን የሶማሌ ክልል ወጣቶችን ድብደባ ሲፈጽሙባቸውና በርካቶችን አፍነው ሲወስዱ እንደነበር ለኢሳት የደረሰው መረጃ አመልክቷል።

ተቃውሞ ዛሬም በሌሎች የክልሉ አካባቢዎች መቀጠሉ ታውቋል።

ሽንሌ ዞን የጀመረውን ህዝባዊ ተቃውሞ በቅርበት ስትከታተል የቆየችው የሶማሌ ክልል ዋና ከተማ ጂጂጋ ዛሬ ተቀላቅላለች።

ጂጂጋ ተቃውሞውን ስትቀላቀል በስራ ማቆም አድማ መሆኑን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

ዛሬ ጂጂጋ ጸጥ ረጭ ብላ ውላለች። ሱቆች ተዘግተዋል። መደብሮች የገበያ ማዕከላት ከእንቅስቃሴ ውጭ ሆነዋል።

ተሽከርካሪዎችም ከመንገድ ላይ አይታዩም። በከተማዋ ከሶማሌ ክልል ልዩ ሃይል ተሽከርካሪዎች በቀር የሚንቀሳቀስ እንዳልነበረ የኢሳት ምንጮች ካደረሱን መረጃ ለማወቅ ተችሏል።

ትላንት በደገሀቡር ዞን ጋሻሞ አካባቢ ጠንካራ ተቃውሞ መደረጉን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ዛሬም በጋሻሞ ተቃውሞ የቀጠለ ሲሆን የክልሉ ታጣቂዎች ህዝቡ ላይ ሲተኩሱ ነበር ተብሏል።

የደረሰውን ጉዳት በተመለከተ ዝርዝር መረጃ አልደረሰንም።

በኤረር ዞን አስቡሊ ትላንት የጀመረው ተቃውሞ ቀጥሎ ዛሬም መካሄዱን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

በዋርዴር ዞን ራሶ በተባለው አካባቢ በተነሳው ተቃውሞ የአብዲ ዒሌ አስተዳደር ሰራተኞች ከአከባቢው ለቀው እንዲወጡ ህዝቡ መጠየቁም ታውቋል።

በሽንሌ ዞን የተጀመረው ተቃውሞ በቅርበት የምትከታትለው ድሬዳዋም ዛሬ ተቃውሞ ተካሂዷል።

ከሶላት ስግደት በኋላ በተካሄደው ተቃውሞ የአብዲ ዒሌ አስተዳደር ከስልጣን እንዲወርድ መጠየቁ ታውቋል።

በሽንሌ ከተማ ዛሬ በተደረገው ተቃውሞ የሶማሌ ልዩ ሃይል ከአጋዚ ሰራዊት ጋር በመሆን ህዝቡ ላይ ርምጃ መወሰዱን ነው የደረሰን መረጃ የሚያመለክተው።

በሽንሌ ከተማ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ምስል ያለበትን ቲሸርት የለበሱ ወጣቶች ላይ ከፍተኛ ደብደባ መፈጸሙን የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።

ከ50 በላይ ወጣቶችም መታሰራቸው ታውቋል። በርካታ መደብሮች የታሸጉ ሲሆን ቲሸርቱን ሲሸጡ ነበር የተባሉ መደብሮች ላይ ትኩረት ተደርጎ ርምጃ መወሰዱ ተገልጿል።

በጂጂጋ በቅርብ ርቀት ላይ ባለችው በጉርሱም ደንሃሌ ዛሬ የተደረገው ተቃውሞ ከፍተኛ እንደነበርም ከደረሰን መረጃ ለማወቅ ተችሏል።

የክልሉ የሚሊሺያ ሰራዊት ከህዝቡ ጋር በተጋጨበት በዛሬው የደንሃሌ ተቃውሞ አንድ አዛውንት በጥይት መመታታቸው ታውቋል።

የሚሊሺያ ሰራዊቱ አንድ ተሽከርካሪም በህዝቡ ጥቃት ተፈጽሞበታል።

በሶማሌ ክልል የተነሳውን ተቃውሞ ለማስቆም የአጋዚ ሰራዊት ጣልቃ መግባቱም እየተነገረ ነው።

በተለይ አዲስ አበባ የሚገኙት የክልሉ ፕሬዝዳንት አብዲ ዒሌ ከህውሀት የጦር ሹማምንት ጋር መወያየታቸውን ተከትሎ የአጋዚ ሰራዊት ከሶማሌ ልዩ ሀይል ጋር በመሆን የህዝቡ ተቃውሞ ለማስቆም መሰማራቱን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።