በጅጅጋ የሚታየው ስረአት አልባነት ተባብሷል

ህዳር (ሃያ አራ)ቀን ፳፻፮ / ኢሳት ዜና :-በጅጅጋ በማንኛውም ሰአት ዜጎች ቤታቸው በጸጥታ ሀይሎች ይፈታሻል። የጸጥታ ሀይሎችም ከሞባይል ስልክ ጀምሮ እስከ ላፕቶፕ እንዲሁም ገንዘብ ይወስዳሉ። የቀበሌ መታወቂያዎችን ሳይዙ ከሄዱ ደግሞ ተጠርጥረው ይያዛሉ። የከተማዋ ነዋሪዎች እንደሚሉት ጅጅጋ ለኢትዮጵያውያን ከሳውድ አረቢያ በላይ የስቃይ መሬት ሆናለች ።

አንድንድ ምንጮች እንደሚሉት ችግሩን የተወሳሰበ ያደረገው አልሸባብ  በጅጅጋው ፕሬዝዳንት የግል ሞባይል ላይ የብሄር ብሄረሰቦች በአል በከተማዋ የሚከበር ከሆነ  እርምጃ እንደሚወስድ መሀላ ያለበት የዛቻ ኤስ ኤም ኤስ መላኩን ተከትሎ

ከፍተኛ ፍተሻ በየጎዳናው እየተደረገ ሲሆን ከነሱ ጋር ግንኙነት አለህ በሚል አንድ የጅጅጋ ነዋሪ ጫካ ተወስዶ  ሲደበድቡት በድንገት በመሞቱ ለቤተሰቡ 50 ሺ ብር ካሳ ተሰጥቶ ሬሳው ከከተማ ውጭ እንዲቀበር ተደርጓል፡፡  ከአልሸባብ ጋር በተያያዘም አንዲት ወጣት ሴት ከአካባቢው ተወስዳ ማእከላዊ ታስራ መደፈሩዋም ታውቋል፡፡

ህዳር 29 የሚከበረውን  የብሄር ብሄረሰቦች ቀን  እንዲሳተፉ የተጋበዙ አንዳንድ የአዲስ አበባ ከተማ አስተደደር የካቢኔ አባላት በጸጥታና ደህንነት ምክንያት ለመሄድ አለመፈለጋቸውንም የደረሰን መረጃ ያመለክታል።  ይህንን ተከትሎም ከፍተኛ ባለስልጣኖች ለካቢኔ አባላት ጠንካራ ደብዳቤ በመጻፍ በስፍራው እንዲገኙ እያዘዙ ነው።

ይህ በእንዲህ እንዳለ  በኢ.ፌ.ዳ.ሪ. የፌዳሬሽን ምክር ቤት እና በኢትዮጵያ ሶማሊ ክልላዊ መንግሥት ትብብር 8ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል አከባበር ለውይይት የቀረበ በሚል ርእስ የተዘጋጀው ጽሁፍ ለኢሳት አስቀድሞ የደረሰው ሲሆን  በጽሁፉ ውስጥ ስለክልሉ ታሪክ አነጋጋሪ የሆኑ ጉዳዮች መካተታቸውን ተመልክቷል።

በጽሁፉ ውስጥ “የአቢሲንያ መኳንንት ወደ በረሃው የሚወርዱት ሊያጋጥም የሚችለውን የወባ በሽታ በሚክስ ደረጃ ፈጣንና ትርፋማ የከብት ዘረፋ ለማድረግ ብቻ ነው፡፡” ለምሳሌ ሽፍቶችን በማጥፋት ስም የአፄ ምኒሌክ ጦር አባላት በ1902 እ.ኤ.አ. ከ50ሺ በላይ የእንስሳት ሀብት ከማኅበረሰቡ ተዘርፎ በጅጅጋ በኩል ወደ ሀረር እንዲላክ ተደርጓል፡፡ ” ይላል።

በኀይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥትም የክልሉ ሕዝቦች እንደ ሌሎች የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በሀገሪቷ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ተገለው የቆዩበት ጊዛ ነበር ካለ በሁዋላ፣ የጭቆና ቀንበራቸውን በመጫንና ሕዝቡን ለመቆጣጠር ጥቂት ለሆዲቸው ለኖሩ የጎሳ መሪዎች የተወሰነ ጊዚያዊ ጥቅም በመስጠትና በማታለል ይንቀሳቀሱ ነበር ብለዋል፡፡ የኢጣሊያ ወራሪ ኀይል ኢትዮጵያን ቅኝ ለመግዛት በሚያደርገው ዝግጅት የተደናገጡት አፄ ኀይለስላሴ በመጀመርያ ጊዜ የክልሉን ታዋቂ ግለሰቦችና የጎሳ መሪዎች ሀረር ላይና በመቀጠል በቀብሪደሀር ከተማ በመሰብሰብ የክልሉ ሕዝብ ሀገሪቷን ከወራሪው ኀይሌ እንዲከላከል ጠይቀው ነበር ጽሁፉ ያመለክታል፡፡ጽሁፉ በኢህአዴግ ዘመን ለክልሉ የተሻለ እድል መምጣቱንም ያትታል።