ታህሳስ ፫(ሦስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የጅጅጋ ወኪል የሆቴል ባለንብረቶችን አነጋግሮ እንደዘገበው በክልሉ የተቋቋመው እና በከፍተኛ ደረጃ የሚፈራው ልዩ ሚሊሺያ የሆቴሎች ባለቤቶችን እያስገደዱ ገንዘብ ይዘርፋሉ። ሚሊሻዎቹ የሆቴል ባለቤቶችን የሚዘርፉት የኦጋዴን አማጽያንን ያለበቂ ፍተሻና ምዘገባ በሆቴላችሁ ታሳድራላችሁ ፣ በቂ የፍተሻ ሰራተኞችን አልመደባችሁም በማለት ነው።
“በመጀመሪያ ሚሊሺያዎች፣ ፖሊሶችና ባለስልጣናቱ ሆቴሎች ውስጥ ገብተው ይቀመጣሉ፣ ከዚያም ይሀው መሳሪያ ይዘን ገብተናል ፣ ፍተሻችሁ ጠንካራ አይደለም ” በማለት ከ1ሺ እስከ 3ሺ ብር የሚደርስ ገንዘብ እንደሚቀጧቸው ወኪላችን ገልጿል።
በሶማሊ ክልል የሚፈጸመው ግፍ ያለተቆጣጣሪ መቀጠሉን ነዋሪዎች በተደጋጋሚ መግለጻቸው ይታወሳል። የፌደራሉ መንግስት በልዩ ሚሊሺያዎች አማካኝነት ስለሚፈጸመው የሰብአዊ መብት ጥሰት እስካሁን ያለው ነገር የለም።