በጅጅጋ በመከላከያ በአል ላይ የአየር ላይ ትርኢት ለማሳየት የነበረው እቅድ ተሰረዘ

የካቲት ፯ ( ሰባት )ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በጅጅጋ በተከበረው የመከላከያ ቀን ላይ በአየር ሃይል ሄሊኮፕተሮች የአየር የበረራ ትርኢት ለማሳየት ታቅዶ የነበረ ቢሆንም በአብራሪዎች ችሎታና የአይሮፕላኖች ቴክኒካዊ ብቃት ጉድለት ምክንያት እንደታሰበው ሳኪያሄድ ቀርቷል።
በአሉ አስቀድሞ በደብረዘይት ከተማ በሚገኘው የአየር ሃይል ዋና አዛዠ በሆነዉ ሰፈር ለማክበር ታስቦ የነበር ሲሆን፣ ዘግይቶ በመጣ ትዕዛዝ በዓሉ በጂጂጋ እንዲከበር መወሰኑን የመከላከያ ምንጮቻችን ገልጸዋል።
የህወሃት ኢህአዴግ አገዛዝ ፣ ሰራዊቱ ለስርዓቱ ያለውን ታማኝነት የሚያድስበትና የሚያጸናበት መልዕክት በበዓሉ ሰበብ ለህዝቡና ለተቋዋሚዎች እንዲተላለፍበት አልሞ የተለያዩ ይዘት ያላቸው ፕሮግራሞችንና ሰልፎችን ለማድረግ ያሰበ ቢሆንም፤ በአየር ሃይል ሄሊኮፕተሮች ታስቦ የነበረው የአየር በረራ ትርኢት ሳይሳካ ቀርቷል።
በመላ ሃገሪቱ ሰፊ ህዝባዊ እምቢተኝነት ከተቀጣጠል ካለፉት 18 ወራት ወዲህ፤ መንግስት የወሰዳቸውን ጸረ ህዝብ እርምጃዎችን አስመልክቶ በተነሱ ጥያቄዎች ምክንያት በሰራዊቱ ውስጥ ከፍተኛ አለመተማመንና መከፋፈል እንደተከሰትና አሁንም መፍትሄ ያላገኘ ችግር እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ። ከዚህ ቀደም ባልተለመደ ሁኔታ ሰራዊቱ አመቺ አጋጣሚዎችን በመጠቀም በቡድንና በግል ግዳጁን እየተው የተቋውሞ ሃይሎችን እየተቀላቀል መሆኑን ከዚህ ቀደም የዘገብን መሆኑ የሚታወስ ሲሆን፤ መንግስት ይህንን ሁኔታ ለማርገብ ሲል በሰራዊቱ ውስጥ ከፍተኛ የቁጥጥርና የስለላ መረቦችን በመዘርጋት የገዛ ሰራዊቱን በመሰለልና በመከታተል ስራ ላይ እንዲጠመድ ግድ ሆኖበታል።
በሽልማት ስነስርዓቱ ላይ ከአፍሪካ ሰላም አስከባሪ ውጭ ሲንቀሳቀስ የነበረውና ከሶማሊያ ለቆ የወጣው የ18ኛው ክፍለጦር አዛዦች መሸለማቸው የሰራዊቱን አባላት በእጅጉ አስገርሟል። “አዛዦቹ ብዙ ጉዳት ያደረሱ ናቸው፣ ለምን እንደተሸለሙ አላውቅም፣ ሰዎችን ያስገደሉ አዛዦች እንዴት ሊሸለሙ ይችላሉ” ሲል አንድ የደህንነት አባል ለኢሳት ተናግሯል።
በዚህ ጉዳይ ከተለያዩ የደህንነት ምንጮች ያገኘናቸውን መረጃዎች አሰባስበን በነገው የዜና ዘገባ ላይ የምናቀርብ መሆናችን ከወዲሁ እንገልጻለን።