በጅጅጋ ለብሄረሰቦች በአል ሲባል ትምህርት ቤቶችና መስሪያ ቤቶች ተዘጉ

ህዳር ፲፯(አስ ሰባት )ቀን ፳፻፮ / ኢሳት ዜና :-በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ጅጅጋ ከተማ ህዳር 29 ቀን 2006 ዓ/ም ለ8ኛ ጊዜ  የሚከበረውን የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች  በዓል  ጋር በተያያዘ የመንግስት ሥራ እና የዩኒቨርሲቲ ትምህርት እንዲቋረጥ ከመደረጉም በላይ በከተማዋ በየእለቱ ቤት ለቤትና በጎዳና ላይ ጥብቅ ፍተሻ እየተከናወነ ነው።

 በጅጅጋ ከበዓሉ ጋር በተያያዘ ከ3ሺ500 በላይ እንግዶችን ታስተናግዳለች ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን እንግዶቹ ከሚያርፉባቸው ቦታዎች አንዱ የጅጅጋ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች ማደሪያ በመሆኑ ዩኒቨርሲቲው ሰሞኑን ለአንድ ወር ትምህርት እንደማይኖር በመግለጽ ተማሪዎቹን ማሰናበቱ ታውቋል፡፡

ተማሪዎቹ ሲሰናበቱ የተሰጣቸው ምክንያት ለተማሪዎቹ ደህንነት ተብሎ ነው በሚል መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በከተማዋ የመንግስት ስራ ይፋ በሆነ መንገድ ከተዘጋ አንድ ወር እንደሚሆነው የጠቆመው ምንጫችን ሁሉም ነገር የብሔረሰቦች በዓል ብቻ ሆኖአል ሲል ገልጾአል፡፡

በጅጅጋ ከተማ ሰሞኑን ለስራ ጉዳይ ሄደው የተመለሱ የአንድ የምግባረ ሰናይ ድርጅት ባልደረባ ለአዲስአበባው ዘጋቢያችን እንደተናገሩት በከተማው በየጎዳናው ድንገተኛ ፍተሻ የሚደረግ ሲሆን ማናቸውም ተሸከርካሪዎች ፣ታክሲዎች በየዕለቱ የሚደረገው ብርበራ በመሰላቸት ብዙዎቹ አገልግሎት አቁመዋል፡፡ ሆቴሎች ሌሊት ጭምር የተኙ እንግዶች በር እየተደበደበ ፍተሻ እንደሚካሄድ የጠቀሰው ምንጫችን የሚታየው ነገር ሁሉ አስፈሪ መሆኑን ተናግሮአል፡፡

አንድ የጅጅጋ ነዋሪም በፍተሻውና በጸጥታ ሃይሎች ወከባ መሰላቸታቸውን በመግለጽ ይህ በዓል ለሶማሌ ህዝብ ያተረፈለት እንግልትና መሳቀቅ በመሆኑ ምነው ባልመጣ እያልን ነው ብለዋል፡፡ በክልሉ የሚንቀሳቀሰው የኦጋዴን ነጻነት ግንባር (ኦብነግ) በዓሉን በማስታከክ ጥቃት ሊያደርስ ይችላል በሚል የክልሉ መንግስት ከፍተኛ ስጋት ውስጥ ይገኛል፡፡