በጅንካ እስር ቤት የሚገኙ የተቃሚ መሪዎች መፍትሄ እንዲሰጣቸው ጠየቁ

ታኅሣሥ ፯ (ሰባት)ቀን ፳፻ / ኢሳት ዜና :- በደቡብ ኦሞ ጅንካ ከተማ ታስረው የሚገኙት የኦሞ ህዝብ ዲሞክራሲያዊ ድርጅት ም/ል ሊቀመንበር መ/ር አለማየሁ መኮንን፣ የዞኑ የድርጅቱ ም/ሊቀመንበር መ/ር እንድሪስ መናን፣ የድርጅቱ የስራ አስፈጻሚ አባላት አቶ ዳዊት ታመነ እና አቶ መሃመድ ጀማል፣ የድርጅቱ አባል አቶ ዘርይሁን ኢቢዞ እንዲሁም አቶ ስለሺ ጌታቸው፣ አቶ አኮ ባይሲኖ፣ አቶ አይሸሹም ወርቁ፣ አቶ አዲሱ ኦርካይዶ፣ አቶ እምነት ጋሻው እና አቶ አባስ አበዱላሂ፣ ታህሳስ 5 ቀን 2009 ዓም ለደቡብ ኦሞ ዞን ኮማንድ ፖስት በጻፉት ደብዳቤ፣“ የሚንስትሮች ምክር ቤት ከ28/01/2009 ዓም ጀምሮ ተግባራዊ ባደረገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የአፈጻጻም መመሪያ መሰረት ነው ተብለን፣ ቤት ንብረታችን ተበርብሮ እና ከመንገድ ላይ በድንገት ተይዘን፣ የተለያዩ የኤሌክትሮኒክስ ቁሳቁሶቻችን ተወስደውብን፣ ከ04/03/2009 ዓም ጀምሮ መኖ፣ ህክምና እና ሌሎች ለቀን ተቀን ህይወት አስፋለጊ የሆኑ ነገሮች በሌሉበት ፣ መጀመሪያ በጂንካ ከተማ ፖሊስ ጣቢያ፣ ቀጥሎ አሁን የምንገኝበት በደቡብ ኦሞ ዞን ፖሊስ መምሪያ በሚገኝ አንድ ክፍል ቤት ውስጥ ከወር በላይ ታስረው እንደሚገኙ አመልክተዋል።

“ የተወሰዱብን የግል ንብረቶቻችን እና ለፓርቲው ስራ መገልገያ ቁሳቁሶች እንጂ፣ በአዋጁ ሁከትና ብጥብጥ ያስነሱ ወይም ሊያስነሱ የሚችሉ ቁሳቁሶች ከማንኛችንም ቤት እና አካል ያልተገኙ በመሆኑ፣ ኮማንድ ፖስቱ በአስቸኳይ ጉዳያችንን አጣርቶ ከተያዙ ንብረቶችና ቁሳቁሶች ጋር የወንጀል ድርጊቶች ተፈጽሟል የሚለው ካለም፣ በማስረጃ በማረጋገጥ ለሚመለከተው ህጋዊ አካል እንዲያቀርበን “ እንጠይቃለን ሲሉ በደብዳቤያቸው ገልጸዋል።

በደቡብ ክልል በተለያዩ ዞኖች በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች በወታደራዊ እዙ ታስረው እንደሚገኙ የሚደርሱን መረጃዎች ያመለክታሉ።