በጅቡቲ ወደብ እቃን የማያነሱ ነጋዴዎች ከንግድ ስራቸው እንዲታገዱ የሚያደርግ መመሪያ ወጣ

ኢሳት ( ግንቦት 1 2008)

ከጎረቤት ጅቡቲ ወደብ እቃን የማያነሱ ነጋዴዎች ከንግድ ስራቸው እንዲታገዱና የውጭ ምንዛሪ እንዲያገኙ የሚያደርግ መመሪያ ተግባራዊ ተደረገ።

አስመጪ ነጋዴዎች በበኩላቸው መንግስት ከንግዱ ማህበረሰብ ጋር በቂ ምክክርን ሳያደርግ እየወሰደ ያለው እርምጃ ተገቢ አይደለም ሲሉ ተቃውሞ ማቅረብ መጀመራቸው ታውቋል።

ባለፈው ሳምንት መንግስት ከጅቡቲ ወደብ ገብተው በደረቅ ወደብ የተቀመጡ እቃዎች ከግንቦት 1, 2008 ጀምሮ እንደሚወረሱ ማስታወቁ የሚታወስ ሲሆን፣ ድርጊቱም በነጋዴዎች ዘንድ ቅሬታን ማስነሳቱ ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።

እቃዎቹን ከመውረሱ እርምጃ በተጨማሪም አስመጪ ነጋዴዎች ከንግድ ስራቸው እንዲታገዱና የውጭ ምንዛሪም እንዳያገኙ የሚያደርግ መመሪያ መውጣቱን የባለስልጣኑ ሃላፊዎች ገልጸዋል።

ይሁንና፣ በንግድ ስራ ላይ የተሰማሩ አካላት ብድር ማግኘት የገበያ መቀዛቀዝ እና ሌሎች ተጓዳኝ ችግሮች እቃዎቻቸውን በወቅቱ እንዳያነሱ እንቅፋት መፍጠሩን በመግለጽ ላይ ናቸው።

የመንግስት አካላትም ይህንን ችግር ግምት ውስጥ ባለማስገባት የወሰደው እርምጃ ተገቢ አለመሆኑን ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ ነጋዴዎች ለመገናኛ ብዙሃን አስረድተዋል።

“ቀድመው ከወሰኑ እዚህ ድረስ ለምን ይጠሩናል?” ሲሉ አንድ ስማቸውን ያልገለፁ ነጋዴ ለጋዜጠኞች አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን በአስመጪ ነጋዴዎች ላይ ኣየወሰደ ያለው እርምጃም በሃገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚያሳድር እነዚሁ ነጋዴዎች ገልጸዋል።