ታህሳስ 23 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት:- ድርጅቱ በፈረንጆች አቆጣጠር ዲሰምበር 30 እና 31 ባደረገው ጉባኤ ፣ ለረጅም አመታት ሲታገልበት የነበረውን የመገንጠል አጀንዳ በመሰረዝ ፣ የኢትዮጵያን ህዝብ ፍላጎትና ጥያቄ የሚመልስ የመታገያ አጀንዳ ማሻሻያ ማድረጉን አስታውቋል።
ግንባሩ ሁሉም የኦሮሞ እና ሌሎችም የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ሀይሎች ይህን አዲስ ራእይ እውን ለማድረግ በጋራ እንዲሰሩ ጥሪ አቅርቧል።
የድርጅቱ ጉባኤ ከመካሄዱ ጥቂት ቀናት በፊት በአቶ ዳውድ ኢብሳ የሚመራው ኦነግ፣ የድርጅቱን ስያሜ ተጠቅሞ የሚካሄድ ጉባኤ ተቀባይነት እንደማይኖረው አስታውቆ ነበር።
የድርጅቱ ሊቀመንበር የሆኑት ጄ/ል ከማል ገልቹ ለኢሳት እንደተናገሩት በአቶ ዳውድ ኢብሳ የሚመራው ክፍል ሀላፊነቱን ከሶስት አመታት በፊት ያስረከበ በመሆኑ ህጋዊ አይደለም
ጄ/ል ከማል ገልጁ እንደሚሉት ሰሞኑን የተካሄደው ጉባኤ የተበታተኑን የኦነግ ሀይሎች አንድ ለማድረግ የሽምግልና ጥረት ከተካሄደ በሁዋላ የማይቻል መሆኑ በመታወቁ የተካሄደ ነው ።
“የእናንተ ጥንካሬ በአቶ ዳውድ ኢብሳ ከሚመራው ኦነግ ጋር ሲነጣጠር ምን ይመስላል?” ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ ጄኔራሉ “የእኛ ሀሳብ የአብዛኛው የኦሮሞ ህዝብ ሀሳብ ነው ብለን እናምናለን።”በማለት መልሰዋል። ጄኔራሉ “ይህ ማለት የእኛን ሀሳብ የማይደግፉ ሰዎች አይኖሩም ማለት አይደለም” ሲሉ አክለዋል።
ድርጅቱ ሲመሰረት ጀምሮ የመታገያ አጀንዳው ምን ይሁን የሚለው ጥያቄ ሲያከራክር መቆየቱን ያወሱት ጄኔራል ከማል፣ ይህ ጥያቄ በአሁኑ ጉባኤ እልባት ማግኘቱንም ገልጠዋል።
የአቶ ዳውድ ኢብሳን መልስ ለማግኘት ሞክረን አልተሳካልንም፣ መልሳቸውን እንዳገኘን ለማቅረብ እንሞክራለን።