ታኅሣሥ ፲፩ (አሥራ አንድ)ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የአካባቢው ነዋሪዎች እንደሚገለጹት ታህሳስ 5 እና 6 በነበረው ሁለተኛ ዙር ተቃውሞ አገዛዙ ሁለት ታንኮችን አስገብቶ የነበረ ቢሆንም፣ ከህዝብ የተሰነዘረበትን ጥቃት መቀነስ ሳይችል ቀርቷል። አርሶአደሮችና ታጋዮች ተቃውሞውን ተከትሎ እነሱን ለማጥቃት የሄደውን አንድ ታንክ እንዳቃጠሉ እየተናገሩ ቢሆንም፣ ኢሳት ከራሱ ምንጮች እስካሁን ለማረጋገጥ አልቻለም። የአካባቢው ዘጋቢያችን እና ከዋና ከተማው ራቅ ብሎ በሚገኘው የጃዊ የሸንኮራ አገዳ የሚሰሩ ሰራተኞችን አናግረን፣ አንደኛው ታንክ አለመመለሱን መስማታቸውን ገልጸዋል።
በአካባቢው ያለውን ውጥረት ተከትሎ የጃዊ ስኳር ፋብሪካ ሰራተኞች ሰናይፐር በታጠቁ ወታደሮች ሌት ተቀን እየተጠበቁ መሆኑን ሰራተኞች ገልጸዋል። የስኳር ፋብሪካውን የሚገነባው ሜቴክ ሃላፊ ወዲ ሃጎስ ተቃውሞው እየከፋ ከመጣ ፋብሪካውን ለቀን እንወጣለን በማለት እያስፈራሩ እንደሚገኙ ሰራተኞች ተናግረዋል።
ሰሞኑን 60 ሄክታር የሸንኮራ አገዳ መቃጠሉ ውጥረቱን አባብሶታል። የአካባቢው አርሶደሮች ተገቢው ካሳ ሳይከፈላቸው የእርሻ ማሳቸውን ለስኳር ፋብሪካው ግንባታ እንዲያስረክቡ መደረጋቸው ለተቃውሞውን መነሻ ምክንያት ሆኗል። የሜቴክ ሃላፊዎች የአካባቢውን አሸዋ በመሸጥ አካባቢውን እያራቆቱ ነው የሚል ክስም በህዝቡ ዘንድ ይቀርብባቸዋል።
ከአካባቢው ህዝብ አብራክ የወጡት የነጻነት ሃይሎች ራሳቸውን አደራጅተው ጫካ በመግባት ከፍተኛ ጉዳት እያደረሱ መሆኑንም ከስፍራው የደረሰን መረጃ ያመለክታል።