በጃዊና አካባቢዋ በተነሳው የህዝብ አመጽ ውጥረቱ እንዳለ ነው

ታኅሣሥ ፯ (ሰባት)ቀን ፳፻ / ኢሳት ዜና :- ከአማራ እና ከቤንሻንጉል ክልሎች በሚዋሰነው የጃዊ ስኳር ፋብሪካ አቅራቢያና የፈንድቃ ከተማ አካባቢ በከፍተኛ ውጥረት ላይ መሆኑን የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡

ሰሞኑን የጃዊ ስኳር ፋብሪካን ድርሻ ሰባ አምስት በመቶ ለቱርክ ባለሃብቶች መሽጡን ተከትሎ በፕሮጀክቱ ለተወሰደባቸው መሬት ተተኪ ቦታ ያላገኙና ምንም አይነት ካሳ ያልተከፈላቸው የአካባቢው አርሶ አደሮች እያነሱት ያለው ቅሬታ ሳይበርድ፤ የሚቴክ ወታደራዊ ባለስልጣናት በግላቸው ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት ባደረጉት እንቅስቃሴ በተከሰተው ችግር በአካባቢው ከፍተኛ ውጥረትና የደም መፋሰስ እንደተከሰተ የክልሉ ዘጋቢያችን ገልጿል።

ከጃዊ ዋና ከተማ ፈንድቃ በስልሳ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው የገጠር ከተማ ለረዥም ዓመታት በአሸዋ ንግድ ተደራጅተው የሚተደደሩትን የአካባቢውን አርሶ አደሮች ስራ፣ የጃዊ አካባቢ ሚቴክ ባለስልጣናት የአሸዋ ንግዱን በመቀማት ለራሳቸው ለመስራት ባደረጉት ሙከራ የተነሳው ግጭት  ከዕለት ወደ ዕለት እተባባሰ መሄዱን የዓይን እማኞች ተናግረዋል።

የአሸዋ ማቅረቡን ስራ በመስራት ላይ ያሉት የህውሃት ባለስልጣናት ስራውን ከተነጠቁት የአካባቢው አርሶ አደሮች ሊደርስባቸው ከሚችለው ጥቃት ለመከላከል አሸዋ ለማስጫን ለሚሄዱት መኪኖች ጥበቃ የሚያደርጉ ስድስት የመከላከያ ሰራዊት አባላትን በመመደብ ለወራት ሽያጭ ሲያካሂዱ እንደ ነበር የዐይን እማኞች ገልጸዋል፡፡

ጃዊ ውስጥ ያልተገባ ስራ በመስራት ተጠቃሚ በመሆን ላይ የነበሩት የሚቴክ ባለስልጣናት ባለፈው ሳምንት ያሰማሯቸው የጥበቃ ወታደሮች ከአርሶ አደሮቹ ጋር በተነሳው ግጭት ህይወታቸው በማለፉ በታንክ የታገዘ የመከላከያ ሰራዊት በመላክ ግጭቱን ማባባሳቸውን እማኞች ተናግረዋል፡፡ በወታደሮች እና በአካባቢው አርሶ አደሮች በተነሳው ሁለተኛ ግጭት እስካሁን ድረስ ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ወታደሮች በተኩስ ልውውጡ ህይወታቸው ማለፉን የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል።

ይህን ተከትሎ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ የሚቴክ ባለስልጣናት የሀገሪቱን ሰራዊት ለግል ጥቅማቸው ማስፈጸሚያ ለማድረግ ከማህል ሃገር ባስመጡዋቸው በርካታ ወታደሮች እና ታንኮች በመታገዝ በአካባቢው አርሶ አደሮች ላይ ጥቃት በመሰንዘር ላይ ናቸው። በአካባቢው በተከሰተው ግጭት ሳቢያ በስኳር ፋብሪካው ውስጥ የሚሰሩ አንዳንድ ሰራተኞችና የአካባቢው ነዋሪዎች ቦታውን እየለቀቁ ወደ መሃል ሀገር እየተጓዙ ሲሆን፤ለስምንት ዓመታት በኢህአዴግ መንግስት ሲከናወን የነበረውን

የስኳር ፋብሪካ ስራ ለቱርክ ባለሃብቶች ለማስተላለፍ የተጀመረው ርክክብ እንዳይደናቀፍ ወደ አካባቢው በክራይ የሄዱ የመንገድ ስራ ድርጅቶች ቀን እና ሌሊት እንዲሰሩ በመገደድ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ በአካባቢው ራሳቸውን አደራጅተው ጫካ የገቡ ወጣቶች መኖራቸውንና ወጣቶችን ለማደን ታንኮችና የጦር መሳሪያዎች ወደ አካባቢው መንቀሳቀሳቸውን ኢሳት ባለፈው ሳምንት ዘግቦ ነበር።

የጃዊ ስኳር ፋብሪካ ንብረት የሆነ60 ሄክታር የሸንኮራ አገዳ በቅርቡ በእሳት መጋየቱን መዘገባችን የሚታወስ ሲሆን፣ ይህንን ተከትሎ መንስኤውን የሚመረምረው በፌደራል ደረጃ የተዋቀረው ሃይል እስካሁን ውጤቱን ይፋ አላደረገም።