ኅዳር ፳፰ (ሃያ ስምንት)ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በዳባት ወረዳ በጃኖራ ቀበሌ ልዩ ስሙ መንደርጌ በተባለው ቦታ ካለፉት 2 ሳምንታት ጀምሮ ሲካሄድ የቆየው ጦርነት ዛሬም እንደቀጠለ ሲሆን፣ በጦርነቱ ላይ የሚሳተፉ ተዋጊዮች እንደሚሉት በአገዛዙ ወታደሮች ላይ ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰ ነው።
በአቶ መሳፍንት ተስፉ የሚመራው የነጻነት ሃይሎች ባለፉት ሁለት ሳምንታት ከ50 በላይ ወታደሮችን መግደሉን የሚገልጹት ተዋጊዮቹ፣ በትናንቱ ጦርነትም ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የስርዓቱ ወታደሮች መገደላቸውንና በርካታ የጦር መሳሪያዎች መማረካቸውን ገልጸዋል።
ቅዳሜ እለት በነበረው ጦርነት በእነሱ በኩል 3 አርበኞች ብቻ መቁሰላቸውንም ተናግረዋል። “ትግሉ አይቆምም፣ ወጣቶችም እየተቀላቀሉን ነው” የሚሉት አርበኛው፣ ከተለያዩ ሃይሎች ድጋፍ እንደሚደረግላቸው ገልጸዋል።
የህወሃት/ኢህአዴግ መንግስት የአቶ መሳፍንትን ሁለት ቤቶች በእሳት ማቃጠሉ መዘገቡ ይታወቃል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በጎንደር ኮሎኔል ደመቀ ዘውዴን ለመያዝ ተደርጎ በነበረው ሙከራ በተኩስ መሃል ለማምለጥ የቻሉትና በአሁኑ ሰአት በትግል ላይ የሚገኙት ከወልቃይት የአማራ ማንነት ጥያቄ አቅራቢዎች መካከል አንዱ የሆኑት ግደይ ርስቀይ አቶ መሳፍንት በጃኖራ እየፈጸሙት ላለው ተጋድሎ አድናቆታቸውን ገልጸዋል።
“ የጎበዝ አለቃው አቶ መሳፍንት በአንድ ቀን 70 የመንግስት ወታደሮችን ያስቀሩ በመሆናቸው 70 ጎራሽ የሚል ስም ሊሰጣቸው ይገባል” ያሉት አቶ ግደይ፣ ጃኖራዎች ከትውልድ ትውልድ የሚያሸጋግሩትን ጀግንነት ደግመውታል ብለዋል።