ታኅሣሥ ፳፯ (ሃያ ሰባት)ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በደቡብ ኦሞ ዞን የሃመር ወጣቶች በጥር 2007 ዓ.ም የጀመሩትን ተቃውሞና ከመንግስት ታጣቂ ኃይሎች ጋር የተፈጠረውን ግጭት ተከትሎ በዞኑ የሚንቀሳቀሰውን የኦሞ ህዝቦች ዲሞክራሲያዊ ኅብረት /ኦህዲኅ/ አመራሮች ለመወንጀል የዞኑ ጸጥታና ደህንነት ሹም/ ኃላፊ አቶ አልዓዛር ቶይሳ የተጀመረው የሃሰት ውንጀላና እስራት እስከዛሬ እንደቀጠለ መሆኑን የድርጅቱ አባላትና የታሳሪዎች ቤተሰቦች አስታወቁ፡፡
አቶ አልኣዛር ባለፈው ዓመት ፣ሚያዚያ 2008 ዓም፣ የኦሞ ህዝቦች ዲሞክራሲያዊ ኅብረት /ኦህዲኅ/- ም/ሊቀመንበር መምህር ዓለማዬሁ መኮንን ፣ የድርጅቱ አባል አቶ አብረሃም ብዙነህ እና የከተማዋን ነዋሪ አቶ ስለሺ ጌታቸው በሽብር ወንጀል እጠረጥራቸዋለሁ በማለት ከቤተሰባቸውና መኖሪያቸው ከ500 ኪ/ሜትር በላይ ተወስደው በሃዋሳ እንዲታሰሩ አድርገው የነበረ ቢሆንም ታሳሪዎቹ ምንም ጥፋት ሳይገኝባቸው በነጻ ተለቀዋል፡፡
አቶ አልዓዛር በድጋሚ በዚህ ዓመት የወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመጠቀም ለክልሉ ኮማንድ ፖስት ‹‹መሰረተ ቢስ መረጃ ›› በመስጠት ከጂንካ ከተማ አልፈው የወረዳ ነዋሪዎችን ጨምሮ ከህዳር 04/2009 ጀምሮ አስራ አንድ የዞኑን ነዋሪዎች አሳስረዋል።
የኦሞ ህዝቦች ዲሞክራሲያዊ ኅብረት /ኦህዲኅ/- ም/ሊቀመንበር መምህር ዓለማዬሁ መኮንን፣ እንዲሁም የዞኑ ሥራ አስፈጻሚ አባል ወጣት ዳዊት ታመነ የእያንዳንዳቸው ቤት በ15 ታጣቂዎች ተፈትሾ ምንም ባልተገኘበት፣ በመቀጠልም የዞኑን ም/ሰብሳቢ መምህር እንድሪስ መናን እና የሥራ አስፈጻሚ አባል ወጣት መሃመድ ጀማል ጨምረው በማሰር የድርጅቱን እንቅስቃሴ እንዲገታ አድርገዋል። እስከዛሬ ድረስ ታሳሪዎች በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መታሰራቸው ከመነገሩ በቀር ‹‹ ይህን አደረጋችሁ ›› ወይም ‹‹በዚህ የወንጀል ድርጊት ተጠረጠራችሁ›› ሳይባሉ በዞኑ ፖሊስ መምሪያ በእስር ላይ ይገኛሉ ፡፡
በታህሳስ 24/ 09 ሁለት ከማዕከል የመጡ የኮማንድ ፖስት አጣሪዎች የእነ አቶ ዓለማዬሁን ጉዳይ ለማጣራት ከዞኑ መድረሳቸውና ስለጉዳዩ ታሳሪዎችን ማነጋገር መጀመራቸው ታውቋል፡፡ ይሁን እንጅ አቶ አለማየሁ በተያዙበት ወቅት ከቤታቸው ተወስዶ ከአንድ ወር ተኩል በላይ በአቶ አላዛር እጅ የሚገኘውን ላፕቶፕ ኮምፑዩተር መረጃ እንፈልጋለን በማለት የኢሜይል እና ፌስቡክ አድራሻቸውን ተቀብለው አቶ ዓለማዬሁ ባሉበት ኮምፒዩተሩን ከከፈቱ በኋላ ባትሪው ደክሟልና ከቤት አስመጣ ብለው አስወጥተዋቸው ፍላሽ ዲስክ በመጠቀም በኮምፒተሩ ውስጥ ያሉትን የግል የሙያም ሆነ ሌሎች መረጃዎች ሁሉ ገልብጠው ወስደዋል፡፡
ታህሳስ 26፣ 2009 ዓም ደግሞ ከኮምፒዩተር መረጃዎችን ሲገለብጡ በድንገት ያገኙዋቸውን አቶ አላዛርን፣ ‹‹ በዚህ መልክ በተቀነባበረ ሴራ የማላውቀው መረጃ ተገኘ ተብሎ ለመወንጀል የተደረገውን በህግ ፊት እንደማልቀበለው ይታወቅልኝ ›› በማለት አቶ አለማየሁ ተናግረዋል።
ይህን የተቀነባበረ መረጃ ሲፈጥሩና በኮምፒዩተር ላይ ሺጭኑ የዞኑ ወንጀል ምርመራ ክፍል አባላት ኢንስፐክተር በኃይሉ ተካ፣ ኢንስፐክተር ትዕዛዙ ምስክር እና ኮንስታብል መልካሙ በቦታው ሆነው ሁኔታውን እንደተመለከቱም የመረጃ ምንጮቹ ገልጸዋል፡፡