በጀርመን የሚገኝ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ማህበር ካህናት አቡነ መርቆርዮስ ወደ መንበራቸው እንዲመለሱ ጠየቁ

ነሀሴ ፳፰ (ሀያ ስምንት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ማህበሩ ነሀሴ 26 ቀን 2004 ዓም በጀርመን አገር ፍራንከፈርት ከተማ ባወጣው መገልጫ ላይ ” እስካሁን ቤተ ክርስቲአኑዋን ለሁለት የከፈለው ጉዳይ በእግዚአብሄር ፈቃድ አንደኛው አባት ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል ስለዚህ አሁን በህይወት ያሉት ቀድሞም ያለአግባብ በመንግስት ሀይል ከስልጣናቸው እንዲወገዱ የተደረጉት አባት ብጹእ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ ወደ መንበራቸው ሊመለሱ ይገባል።

ማህበሩ ያለፈው ስህተት እንዳይደገም ባለታሪካዊነቷና ጥንታዊነቷ ቤተክርስቲያን ታላቅ የታሪክ ጠባሳ ለትውልዱ እንዳይተላለፍ  አሳስበው፣ አሁን በስደት ላይ ያሉት አባት ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ  በስቸኳይ ወደመንበራቸው እንዲመለሱ ፣ የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት በፍጹም ፍቅርና አንድነት የተጣለባቸውን  መንፈሳዊ ግዴታ በመወጣት የቤተ ክርስቲያኒቷን ችግር ለአንድ ጊዜና ለመጨረሻ ጊዜ እንዲያስወግዱ ፤ እንዲሁም ቤተ ክርስቲያንን እንዲጠብቁ እና ከታሪክ ተጠያቂነት እንዲድኑ ጠይቀዋል።

 

ማህበሩ  በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ የተጋረጠው ችግር ሳይፈታ ለሹመት የሚሯሯጡትን የቤተ ክርስቲያንና የሀገር  ጠላቶች በጽኑ እንቃወማለን የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት፤ አባቶች ካኅናት፤ዲያቆናት፤የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች መላው ህዝበ ክርስቲያን የቤተ ክርስቲያን ቀኖና እንደቀድሞው እንዲስተካከል ፤  መንግሥት እስካሁን በቤተ ክርስቲያኗ ላይ የሠራውን ስህተት አርሞ እጁን ከቤተ ክርስቲያኗ ላይ በማንሳት ለቤተ ክርስቲያኗ አንድነት የሚደረገውን ጥረት እንዲደግፍና በስደት ያሉት ፓትርያርክ ወደመንበራቸው ተመልሰው መለያየት ተወግዶ ሁሉም ለአንዲት ኢትዮጵ በጋራ እንዲረባረብ እንቃፋት ከመሆን እንዲታቀብ እንጠይቃለን ብሏል።

መግለጫው በመጨረሻም ” በኢትዮጵያ የሚገኙ የፖለቲካና የኅሊና እሥረኞች ሕገ መንግሥታዊ መብታቸው ተከብሮ ከሥር ተፈትተው እንደማንኛውም ኢትዮጵዊ ዜጋ በሀገራቸው ጉዳይ ላይ ሀሳባቸውን በነጻነት እንዲገልጹ እንጠይቃለን፤  በአሁኑ ሰዓት አገሪቱን እየመራ ያለው መንግሥት ከመቼውም በላይ ለሰላም በመነሳት እና ከተቀዋሚዎች ጋር በመስማማት ብሔራዊ እርቅ ሁኖ ሰላም እንዲመሠረቱና ሀገራችንን የሰላም ቀጠና በማድረግ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ተቻችሎና ተከባብሮ በመኖር አብሮ የመኖር ራእያችን  እውን እንዲሆን ፈቃደኝነትን እንዲያሳዩ  እናሳስባለን “” ብሎአል