በጀርመንና ኔዘርላንድ የአየርና የየብስ ትራንስፖርት ተቋረጠ  

 

(ኢሳት ዲሲ–ጥር 10/2010)

በአውሮፓ ሃገራት ጀርመንና ኔዘርላንድ የተከሰተው ከፍተኛ አውሎ ነፋስ፣የአየርና የየብስ ትራንስፖርት አገልግሎትን መግታቱ ተገለጸ።

በአውሮፓ መንገደኞች ከሚበዙባቸው አውሮፕላን ማረፊያዎች አንዱ የሆነው የኔዘርላንዱ ሲኪፖል የአውሮፕላን ማርፊያ አገልርግሎቱ ተስተጓጉሏል።

ከከባዱ አውሎ ንፋስ ጋር በተያያዘም የህንጻው ጣሪያዎች መነቃቀላቸው ታውቋል።

በሰአት 140 ኪሎ ሜትር ወይንም 90 ማይል የሚጓዘው አውሎ ንፋስ ዛፎጭን እየገነዳደሰ የባቡር መስመሮች ላይ በመጣሉ የባቡር አገልግሎት ጭምር እንዲቋረጥ አድርጓል።

አንዳንድ የኔዘርላንድ ከተሞች ሙሉ በሙሉ የትራንስፖርት አገልግሎት የተቋረጠባቸው ሲሆን ነዋሪውም በቤቱ እንዲወሰን ፖሊስ አስጠንቅቋል።

በትንሹ 17 የጭነት ተሽከርካሪዎች በሃይለኛው አውሎ ንፋስ ተመተው ተገልብጠዋል።

ይህው ከባድ አውሎ ንፋስ በጀርመን ኖርዝ ራሂን ዌስትፌሊያ በተባለው ግዛትና አጎራባች አካባቢዎች ሙሉ በሙሉ የባቡር ትራንስፖርት እንዲቋረጥ ያደረገ መሆኑ ታውቋል።

በሕንጻዎች ላይ የመሰንጠቅ አደጋ መድረሱም ተዘግቧል።

በትላልቆቹ የጀርመን ከተሞች ቦንና ኮሎኝ የበረራዎች መሰረዝ የተከተለበት ይህ አውሎ ንፋስ ከአየርና ከየብስ ትራንስፖርት ባሻገር የባህር ትራንስፖርቶችንም ማወኩን ቢቢሲና ዋሽንግተን ፖስትን ጨምሮ የተለያዩ አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

የኔዘርላንዱ ስኪፕሆል አውሮፕላን ማረፊያ በማህበራዊ ገጹ ባወጣው ማስታወቂያ ተጓዦች ሁኔታውን በትዕግስት እንዲጠባበቁ አሳስቧል።

አውሎ ንፋሱ ጉዞ ከማስተጓጎሉ ባሻገር የመንገደኞችን ማስተናገጃ ሕንጻ ከፊል ጣራዎችን መንቀሉንም አስታውቋል።

በመሆኑም ካሉት ሶስት የመንገደኛ ማስተናገጃ መግቢያዎች ሁለቱ ስራ በማቆማቸው ሁሉም ተጓዦች በአንድ በር ብቻ እንዲጠቀሙም ትዕዛዝ ሰቷል።

ሌላው ኬ ኤል ኤም የተባለው የኔዘርላንድ አውሮፕላን ማረፊያ ከ230 በላይ በረራዎችን ለመሰረዝ ተገዷል።

“ኮድሬድ” የሚል ስያሜ የተሰጠውና ጀርመኖች ፍሬዴሪክ ብለው የሰየሙት ይህ አውሎ ንፋስ በጀርመን አንድ የ59 አመት ሰው ሲገድል በኔዘርላንድ በትንሹ ሁለት ሰዎች ሞተዋል።

ሁለቱም ሟቾች የ62 አመት ዕድሜ ያላቸው ሲሆን አንዱ መኪናቸው ላይ ዛፍ ወድቆባቸው ሲሞቱ ሌላኛው በዛፍ ቅርንጫፍ ተመተው ህይወታቸው አልፏል።

አውሎ ንፋሱ በጀርመን ከአንድ መቶ ሺ በላይ ሰዎችን ያለመብራት ያስቀረ ሲሆን በአጎራባች ሀገራትም ንፋሱ ባሳደረው ተጽእኖ በሩማንያ 32 ሺ ሰዎች ከኤሌክትሪክ አገልግሎት ውጪ ሆነዋል።