በዶ/ር አብይ አህመድ የሹሙት ስነስርዓት ላይ አንዳንድ እንግዳ ነገሮች ተፈጥረው እንደነበር ጉዳዩን በቅርብ ሲከታተሉ የነበሩ ወገኖች ገልጹ
(ኢሳት ዜና መጋቢት 25 ቀን 2010 ዓ/ም) “አብይ አህመድ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኖ ተመርጦ ከማየው ብሞት ይሻለኛል” ብለው አብይ አህመድ በተገኙበት የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ስብሰባ ላይ የተናገሩት የመንግስት የፓርላማ ተጠሪው አቶ አስመላሽ ወልደስላሴ፣ በበአሉ ላይ መገኘታቸው ብዙዎችን አስገርሞ ነበር።
የህወሃት ዋና ዋና የሚባሉ አመራሮች ከበአሉ በሁዋላ እርስ በርስ እንኳ ለመነጋገር ፍላጎት አጥተው በተከፋ ስሜት ውስጥ እንደነበሩ የገለጹት እነዚህ ምንጮች፣ የኦህዴድና የብአዴን ሙሉ አባላት እና የደኢህዴን የተወሰኑ አባላት ህወሓትን ለማናደድና ለማበሳጨት በሚመስል መልኩ ድጋፋቸውን ከእጅ ጭበጨባ አሻግረው የተደገፉበትን ጠረጴዛ ወደ መደብደብ መሸጋገራቸውን፣ በተለይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ጥቂቶች እየዘረፉ ብዙሃኑ የሚቸግርበትን አካሄድ ማስቀረት አለብን”” ሲሉ በቤቱ ውስጥ ለህወሓት አባላት የተሰጠ የአሽሙር ጉርምርምታና “”ልክ ነው ልክ ነው” የሚል ድምጽ በአዳራሹ ሙሉ በሙሉ መሰማቱን ገልጸዋል።
ምክር ቤቱ በሹመት ስነስርዓቱ ላይ የምክር ቤት አባላት ሳይሆኑ ሶስት ሴት የፌዴሬሽን ምክር ቤት ጽ/ቤት ተራ ሰራተኞች ወደ ስብሰባ አዳራሹ ገብተው ወንበር ይዘው ስብሰባውን ሲከታተሉ ተገኝተዋል። ሴቶቹ እንዴት ብለው ደህንነቱን÷ የአደራሽ ዘበኞችን እና ባለሙያዎችን አልፈው እንደገቡ አልታወቀም። እንግዶችና የጠቅላይ ሚኒስትሮቹ ባለቤቶች እንኳ ወደ ማይገቡበት የስብሰባ አዳራሽ መቀመጫ ወንበር ላይ እንዴት ብለው ሊገቡ÷ ሊቀመጡ ብሎም ሊሳተፉ ቻሉ የሚለው ትልቅ ትርምስ ፈጥሮ ማለፉን፣ በተለይ የሴቶቹ ምስል ግድግዳ ላይ በተሰቀለው ቴሊቪዝኖች ሲመለከቱ በመደናገጥና በመደናገር የፓርላማ አባላቱ ማን ናቸው በሚል ጥያቄ እርስ በርስ ሲጠያየቁ መታየታቸውን ገልጸዋል። በሁኔታው ከልክ በላይ የተበሳጩት የምክር ቤት አባላት ለጽ/ቤቱና ለአፈጉባኤ አቤት ማለታቸውም ታውቋል። ለድህነታቸው እየሰጉ እንደሆነም ገልጸዋል።