ግንቦት ፬ ( አራት ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ሎስ አንጀለስ ሴንቲኔል፣አፍሪካን ኒውስና በርካታ የውጪ ሚዲያዎች ፣ ኢትዮጵያን በመወከል የዓለም የጤና ድርጅት ዳይሬክተር ለመሆን የሚወዳደሩት ዶክተር ቴዎድሮስ አድኃኖም በኢትዮጵያውያን ዘንድ የተቀናጀና ተከታታይ የተቃውሞ ዘመቻ እየተካሄደባቸው እንደሆነ አስነብበዋል።
ዶክተር ቴዎድሮስ አድኃኖምን በማስተዋወቁ ረገድ ከአንዳንድ አካላት ድርጅቱን ለመምራት ብቃት እንዳላቸው ቢገለጽም፣ በበርካታ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ብቁ አይደሉም የሚል ተቃውሞ እንደገጠማቸው ተገልጿል።
በተለይ ተቃውሞውን ያከፋው ፣ዶክተር ቴዎድሮስ ከፍ ያለ የሰብ ዓዊ መብት ጥሰትና ጭቆና በዜጎቹ ላይ የሚፈጽመው የኢትዮጵያ መንግስት ዋነኛ ሰው መሆናቸው እንደሆነ መገናኛ ብዙሀኑ ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት የሰብዓዊ መብት አያያዝ ሁኔታ ሂዩማን ራይትስ ዎችን፣ አምነስቲ ኢንተርናሽናልን፣ ፍሪደም ሀውስን ጨምሮ በበርካታ የመብት ተሟጋቾች ዘንድ በደንብ ተመዝግቦ የሚገኝ መሆኑን ያወሱት ሚዲያዎቹ፣ በዩናይትድ ስቴትስ ስቴት ዲፓርትመንትም በዓመታዊ የሰብዓዊ መብት አያያዝ ሪፖርት ላይ ሰፍሮ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ዶክተሩን የመቃወሙ ዘመቻ ትዊተርና ፊስቡክን ጨምሮ በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች ተጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን፤ የፊታችን ጁላይ 22 በስዊዘርላንድ ጄኔቫ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጽህፈት ቤት ፊት ለፊት አውሮፓ አቀፍ ሰልፍ ተጠርቷል።
የቀድሞው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር አመራር አቶ አሚን ጁዲ ሰሞኑን በሰጡት ቃለ ምልልስ የዶክተር ቴዎድሮስ ለዓለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተርነት መታጬት ለኢትዮጵያውያን ስድብ መሆኑን በመጥቀስ፤ የተጀመረው የተቃውሞ ዘመቻ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል።