ግንቦት ፲ ( አሥር ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በህወሃት/ኢህአዴግ አገዛዝ ውስጥ በጤና ጥበቃ እና በውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ያገለገሉት ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም፣ ገዢው ፓርቲ፣ ታላላቅ አለማቀፍ ሃብታሞች የሚያፈሱትን የገንዘብ ድጋፍ እንዲሁም የአፍሪካ ህብረትን እርዳታ በመተማመን የአለም የጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ሆነው ለመመረጥ ከፍተኛ ዘመቻ እያካሄዱ ሲሆን ፣ በተቃራኒው ደግሞ በአገዛዙ ከፍተኛ በደል የደረሰባቸው ኢትዮጵያውያን የግለሰቡን መመረጥ አጥብቀው በመቃወም ከፍተኛ ዘመቻ ጀምረዋል።
ኢትዮጵያውያኑ የዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም መመረጥ ለአመታት እርሳቸውና ድርጅታቸው በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ የፈጸሙትን ከፍተኛ ወንጀል እውቅና እንደመስጠት ይቆጠራል በማለት በፌስቡክ፣ በትዊተር ተቃውሞአቸውን እየገለጹ ነው። ግለሰቡ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በነበሩት ወቅት የሚባልላቸውን ያክል ለውጥ አለማምጣታቸውን ማስረጃዎች እየጠቀሱ የሚሞግቱት ኢትዮጵያውያን፣ የአለማቀፉ ማህበረሰብ ግለሰቡን የድርጅቱ መሪ አድርጎ እንዳይመርጥ ጥሪ እያቀረቡ ነው።
ተቃውሞው የአለማቀፍ እውቅና ያላቸውን ኒዮርክ ታይምስና ዋሽንግተን ፖስት የተባሉትን ጋዜጦች ትኩረት የሳበ ሲሆን፣ ሁለቱም ጋዜጦች በጉዳዩ ላይ ሰፊ ዘገባ ይዘው ቀርበዋል። ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም፣ በኢትዮጵያ ተከስተው የነበሩና አሁንም የተከሰተውን የኮሌራ ወረርሽኝ በስም ላለመጥራት ለበሽታው ውሃ ወለድ በሽታ የሚል ስያሜ እንዲሰጠው አድርገዋል የሚል ክስ የተሰነዘረባቸው መሆኑን ሁለቱም ጋዜጠኞች በስፋት አትተው ጽፈዋል።
ኢትዮጵያኖች ምርጫው በሚካሄድበት እለት የፊታችን ሰኞ ሜይ 22፣ 2017 በጄኔቭ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጽ/ቤት ፊት ለፊት የዶ/ር ቴዎድሮስን መመረጥ ለመቃወም ሰልፍ አዘጋጅተዋል። የኢትዮጵያ ኢምባሲም በተመሳሳይ ለዶ/ር ቴዎድሮስ ድጋፍ ሰልፍ ማዘጋጀቱ ታውቋል።
ገዢው ፓርቲ በዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም አማካኝነት ለአይ አይ ቪ /ኤድስ ስርጭት መቆጣጠሪያ ተብሎ የተመደበውን ገንዘብ ለፓርቲው ስራ ማዋሉን በርካታ የግል የመገናኛ ብዙሃን ሲዘግቡት ቆይተዋል።
ዶ/ር ቴዎድሮስ የቲማቲም እርሻን ጨምሮ ሌሎች በርካታ የንግድ ድርጅቶች አሉዋቸው። ለኢትዮጵያ የህክምና እርዳታ ለማድረግ የመጡ ቢል ጌትን የመሳሰሉ ባለሃብቶችንና የቀድሞውን የአሜሪካ መሪ ጆርጅ ቡሽን የመሳሳሉ ታዋቂ ሰዎችን በማስተናገዳቸው ድጋፍ ያገኙት ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም፣ ሰሞኑን የሚደርስባቸውን ተቃውሞ “ ከቅኝ ግዛት አስተሳሰብ” ጋር በማያያዝ ተቀናቃኞቻቸውን በመወንጀል አፍሪካውያን ድጋፋቸውን እንዳይነፍጉዋቸው ቅስቀሳ እያደረጉ ነው።