በዶ/ር መረራ ላይ የተሰረተው ክስ ፖለቲካዊ ተልዕኮ ያለው ነው ሲል ሂውማን ራይስት ዎች ስጋቱን ገለጸ

ኢሳት (የካቲት 21 ፥ 2009)

በዶ/ር መረራ ጉዲና ላይ ሰሞኑን የተመሰረተው ክስ ከህግ ይልቅ ፖለቲካዊ ተልዕኮ ያለው ነው ሲል ሂውማን ራይትስ ዎች ማክሰኞ ስጋቱን ገለጸ።

የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቱ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) አመራሩን ጨምሮ ሁሉም የፖለቲካ ዕስረኞች እንዲለቀቁ ጥሪውን ለኢትዮጵያ መንግስት ያቀረበ ሲሆን መንግስት ከህዝብ ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽን ከመስጠት ይልቅ እየወሰደ ያለው እስራት እና ወከባ መፍትሄን እንደማያስገኝ በተመራማሪው ፊሊክስ ሆንር የተጠናቀቀው የሰብዓዊ መብት ድርጅት ሪፖርት ያስረዳል።

ከሶስት ወር በፊት የአስቸኳይ ጊዜውን ተላልፈው ተገኝተዋል የተባሉት ዶ/ር መረራ ጉዲና ከአርበኞች ግንቦት ሰባት ሊቀመንበር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ እንዲሁም ከኦሮሞ ሚዲያ ኔትወርክ ሃላፊ አቶ ጀዋር መሃመድ ጋር ህገመንግስቱን በሃይል ለመናድ እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል ለአመት ከዘለቀው ህዝባዊ ተቃውሞ ጋር እጃቸው አለበት በሚል ክስ እንደተመሰረተባቸው ይታወሳል።

ይሁንና በጉዳዩ ዙሪያ መግለጫን ያወጣው ሂውማን ራይትስ ዎች ክሱ ፖለቲካዊ ተልዕኮ ያለው መሆኑ እና በኦሮሚያ ክልል ሲካሄድ የቆየው ህዝባዊ ተቃውሞ ለፓርቲ አመራሮችና አባላት እስራት መንስዔ መሆኑን አውስቷል።

መንግስት በክልሉ ለተቀሰቀሰው ህዝባዊ ተቃውሞ ዕልባት እንደሚሰጥ በተደጋጋሚ ቃል ቢገባም ዕርምጃ ከመውሰድ ይልቅ በፖለቲካ አመራሮችና አባላት ላይ ፖለቲካዊ ተልዕኮ ያለው ክስ በመመስረት ላይ እንደሚገኝ ሂውማን ራይትስ ዎች የተለያዩ መረጃዎችን በማስደገፍ ባወጣው መግለጫ አስፍሯል።

ይኸው በተለያዩ የሃገሪቱ ክልሎች እየተወሰደ ያለው ዕርምጃ ጥልቅ ተሃድሶን አካሄዳለሁ በሚለው የኢትዮጵያ መንግስት ላይ ስጋትን እና ጥርጣሪውን አሳድሮ መቀጠሉን የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቱ አመልክቷል።

ከጥቅምት ወር ጀምሮ ተግባራዊ ተደርጎ የሚገኘው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅም አፈናዎችን አጠናክሮ ለመቀጠል መሳሪያ ሆኖ ማገልገሉንም መቀመጫውን በዚሁ በአሜሪካ ያደረገው ተቋም አክሎ ገልጿል።

በአሁኑ ወቅትም በ10ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ለእስር መዳረጋቸውንና ለህዝባዊ ተቃውሞ ምክንያት የሆኑ የማህበረሰቡ ጥያቄዎች ዕልባት አለማግኘታቸውን ሂውማን ራይትስ ዎች ሰሞኑን ለፍርድ ቤት የቀረበውን ክስ አስመልክቶ ባወጣው መገለጫው አመልክቷል።

ጠቅላይ አቃቤ ህግ ዶር መረራ ጉዲና በአውሮፓ ጉብኝታቸው ከፕ/ር ብርሃኑ ነጋ መገናኘታቸው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የተላለፉት ድርጊት እንደሆነ ለፍርድ ቤት ባቀረበው ክስ አመልክቷል።

የ60 አመቱ የኦፌኮ አመራር የተመሰረተባቸው ክስ ፖለቲካዊ መሆኑን የገለጸው ሂውማን ራይትስ ዎች፣ በኦሮሚያ ክልል ተቀስቅሶ ከነበረው ህዝባዊ ተቃውሞ ጋር በተገናኘ ለእስር ተዳርገው የሚገኙ እስረኞች በአስቸኳይ እንዲለቀቁ ሲል ጥያቄውን ለመንግስት አቅርቧል። መንግስት ለዚሁ ጥሪ የሰጠው ምላሽ የለም።