ኢሳት (የካቲት 24 ፥ 2009)
ጠቅላይ አቃቤ ህግ ሰሞኑን በዶ/ር መረራ ጉዲና፣ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ እንዲሁም በኢሳትና በኦሮሚያ ሚዲያ ኔትዎርክ ላይ የመሰረተውን ክስ ሃሙስ ለችሎት ማሰማት ጀመረ።
ባለፈው ሳምንት ፍርድ ቤት መቅረብ ያልቻሉ ዶ/ር መረራ ጉዲና በችሎት የተገኙ ሲሆን፣ የቀረበባቸውን ሽብርተኛ ቡድን መደገፍ ኣንዲሁም በማነሳሳት በዋና ወንጀል አድራጊነት ተከፋይ በመሆን የሽብር ወንጀል ክስ እንደተነበበላቸው የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል። ዶ/ር መረራ ወደ ችሎት ሲገቡ እስረኞች ከመቀመጫቸው ተነስተው እንደተቀበሏቸውም ከአዲስ አበባ የመጣው ዜና ያስረዳል። ችሎቱ ፕሮፌሰር ብርሃኑ፣ አቶ ጀዋር መሃመድ፣ ኢሳትና፣ ኦኤምኤን በጋዜጣ እንዲጠሩ ትዕዛዝ ወጥቷል።
የኦፌኮ አመራር የፖለቲካ ድርጅታቸውን እንደ ፋሽን ተጠቅመው የፖለቲካው፣ የሃይማኖታዊ ወይም የአይዲዮሎጂ አላማን ለማራመድ በማሰብ በመንግስት ላይ ተፅዕኖን በማሳደር የሃገሪቱን ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ለማናጋትና ለማፍረስ በማቀድ ተንቀሳቅሰዋል ሲል ጠቅላይ አቃቤ ህግ በክሱ አመልክቷል።
በኦሮሚያ ክልል ሲካሄድ የቆየው ህዝባዊ ተቃውሞ እንዲባባስ አድረገዋል የተባሉት ዶ/ር መረራ ጉዲና በአጠቃላይ በመንግስት ተቋማት ከ215 ሚሊዮን ብር በላይ ንብረት መውደምና መንግስታዊ ባልሆኑ ተቋማት ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ የንብረት ጉዳት እንዲደርስ ማድረጋቸው ተጠቅሷል።
ተከሳሹ ዶ/ር መረራ በንብረት ላይ ለደረሰው ጉዳት ተጠያቂ መሆናቸውን የገለጸው ጠቅላይ አቃቤ ህግ በኦሮሚያ ክልል ከተቃውሞ ጋር በተገኛኘ ህይወታቸው ላለፉ ሰዎችም ምክንያት መሆናቸው በክሱ አስፍሯል።
ይሁንና የንብረት ጉዳቱን በቁጥር ያስቀመጠው ከሳሽ አቃቤ ህግ፣ ተከሳሽ በምን ያህል የሰዎች ህይወት ተጠያቂ ሊሆን እንደሚችሉ የሰጠው ዝርዝር መረጃ የለም። መንግስት በኦሮሚያ ክልል ሲካሄድ ከቆየው ህዝባዊ ተቃውሞ ጋር በተገኛኘ 500 ሰዎች እንደሞቱ ማረጋገጡ የሚታወስ ነው።
አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች በወሰዱት የሃይል ዕርምጃ ከ700 የሚበልጡ ሰዎች መገደላቸውን ሲገልፁ መቆየታቸው አይዘነጋም።
አሜሪካና የአውሮፓ ህብረት የጸጥታ ሃይሎች የፈጸሙት ግድያ በገለልተኛ አካል ማጣራት እንዲካሄድበት ጥያቄን ቢያቀርቡም መንግስት ፈቃደኛ እንደማይሆን ምላሽን ሰጥቷል። የሽብርተኛ ቡድን በመደገፍ እና በማነሳሳት በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ መሆን በሚል የሽብርተኛ ወንጀል ክስ የተመሰረተባቸው ዶ/ር መረራ ጉዲና በጠበቃቸው አማካኝነት ክሱ ላይ መቃወሚያ እንዳላቸው ለችሎት አቅርበዋል።
ተመሳሳይ ክስ በሌሉበት የቀረበባቸው ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፣ አቶ ጀዋር መሃመድ እንዲሁም ኢሳትና የኦሮሞ ሚዲያ ኔትዎርክ ድርጅቶች እስከ የካቲት 30, 2009 አም በጋዜጣ ጥረ እንዲደረግላቸው ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል።
ዶ/ር መረራ ጉዲና ከአውሮፓ ፓርላማ የቀረበላቸውን ጉብኝት አጠናቀው ወደ አዲስ አበባ እንዲመለሱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተላልፈዋ ተብለው በቁጥርር ስር መዋላቸው ይታወሳል። ጠቅላይ አቃቤ ህግ ተከሳሽ አዋጁን በመተላለፍ ህዳር 2 ፥ 2009 አም በቤልጂየም ብራሰልስ በኢትዮጵያ ፓርላማ በሽብርተኛ ከተፈረጀው የአርበኞች ግንቦት ሰባት መሪ ጋር ተገኛኝተው ውይይት አካሄደዋል በማለት በክሱ አቅርቧል።
ሂውማን ራይትስ ዎች በበኩሉ ዶ/ር መረራ ጉዲና የቀረበባቸው ክስ ፖለቲካዊ ተልዕኮ ያለው ነው በማለት በአስቸኳይ እንዲለቀቁ ሰሞኑን ጥሪ ማቅረቡ ይታወሳል።
የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ለየካቲት 30, 2009 አም ተለዋጭ ቀጠሮ መስጠቱም ታውቋል።