(ኢሳት ዲሲ–ግንቦት 16/2010) በሶማሌ ክልል በዶሎ አዶ ከተማ በተነሳው ህዝባዊ ተቃውሞ 3 ሰዎች መገደላቸው ተገለጸ።
የክልሉ ልዩ ሃይል በወሰደው ርምጃ ከተገደሉት በተጨማሪ ሰባት ሰዎች ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰባቸው ለማወቅ ተችሏል።
ሁለተኛ ወሩን እያገባደደ ያለው የሶማሌ ክልሉ ህዝባዊ ተቃውሞ ዛሬም በተለያዩ የክልሉ ከተሞች መቀጠሉን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
በሌላ በኩልም በክልሉ በሚገኙ ሁለት ጎሳዎች መካከል ግጭት ተቀስቅሶ ሁለት ሰዎች መገደላቸው ታውቋል።
በአብዲ ኢሌ የሚመራው የክልሉ አስተዳደር ተቃውሞውን አቅጣጫ ለማሳት በሶማሌ የኢትዮጵያ ተወላጆች መካከል የእርስ በእርስ ግጭት እንዲፈጠር እየተደረገ በመሆኑ ህዝቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ የሀገር ሽማግሌዎች ጥሪ አድርገዋል።
በሶማሌ ክልል የተጀመረው ተቃውሞ ቀጥሎ ከትላንት ጀምሮ በሊብን ዞን ዶሎ ኦዶ ከተማ ህዝባዊ ንቅናቄ እየተካሄደ ነው።
በከተማዋና በዙሪያ የሚገኙ ነዋሪዎች የአብዲ ዒሌ አስተዳደር በአስቸኳይ ስልጣን እንዲለቅ የሚጠይቀውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተቀላቅለዋል።
ትላንት ከቀትር በኋላ የተጀመረው ተቃውሞ ዛሬም የቀጠለ ሲሆን በአብዲ ዒሌ የሚታዘዘው ልዩ ሃይል በወሰደው እርምጃ ሶስት ሰዎች መገደላቸውን የኢሳት ምንጮች ካደረሱን መረጃ ለማወቅ ተችሏል።
የልዩ ሃይል አባላት ለተቃውሞ አደባባይ በወጣው ህዝብ ላይ ፊት ለፊት ሲተኩስ እንደነበረ የጠቀሱት የኢሳት ምንጮች ከተገደሉት በተጨማሪ ሰባት ሰዎችም ክፉኛ መቁሰላቸውን ገልጸዋል።
የዶሎ አዶ ከተማና አከባቢዋ በዛሬው ዕለት ከእንቅስቃሴ ውጪ ሆና የዋለች ሲሆን ትራንስፖርትና የንግድ መደብሮች ተዘግተው እንደነበርም ለማወቅ ተችሏል።
የአብዲ ዒሌ ልዩ ሃይል ተጨማሪ ሃይል ወደ ከተማዋ በማስገባት ህዝቡን በድብደባና እስር እያዋከበ መሆኑም ታውቋል።
ከሊበን ዞን ሌላ በሌሎች የክልሉ ዞኖችም ውጥረቱ የበረታ መሆኑን የሚደርሱን መረጃዎች አመልክተዋል።
በትላንትናው ዕለት በቱሊ ጉሌድ ከተማ የገሪና ጃርሶ ጎሳዎች የእርስ በእርስ ግጭት አድርገው ሁለት ሰዎች ተገድለዋል።
የአብዲ ዒሌ አስተዳደር በህዝብ የተነሳባቸው ተቃውሞ ለማጥፋት ከሚወስዱት የሃይል እርምጃ በተጨማሪ በሶማሌ ጎሳዎች መካከል የእርስ በእርስ ግጭት እንዲፈጠር በማድረግ ላይ መሆናቸውንም የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።
በአብዲ ዒሌ አስተዳደር በኩል ከህወሀት ጋር በመሆን የህዝብን ተቃውሞ አቅጣጫ ለማሳት እየተደረገ ያለው የተቀነባባረ ሴራን ህዝቡ ካላከሸፈው አደጋው ከባድ ነው የሚሉት የሀገር ሽማግሌዎች በሌሎች የሶማሌ ክልል አከባቢዎች ተመሳሳይ የጎሳዎች ግጭት ለመቀስቀስ እየተሰራ በመሆኑ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲደረግ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በቱሉ ጉሌድ ከተማ የተቀሰቀሰው የሁለቱ ጎሳዎች ግጭት ዛሬ ረገብ ያለ ቢሆንም ዳግም ሊከሰት እንደሚችል ስጋት መኖሩን የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።
በሽንሌ ዞን ተጀምሮ በ11ዱም የሶማሌ ክልል ዞኖች የተዳረሰው ህዝባዊ ተቃውሞ የዛሬውን ጨምሮ 23 ሰዎች የተገደሉ ሲሆን ከ1ሺህ በላይ ሰዎች ታፍነው ተወስደዋል።
የአብዲ ዒሌ አስተዳደር ለሶማሌ ክልልም ሆነ ለተቀረው የኢትዮጵያ ህዝብ ሰላም ጠንቅ በመሆናቸው በአስቸኳይ ከስልጣን እንዲነሱ በመጠየቅ ለአቤቱታ አዲስ አበባ የገቡት ከ150 በላይ የሀገር ሽማግሌዎች የሚያናግራቸው የመንግስት ባልስልጣን ሳያገኙ ከአንድ ወር በላይ ሆኗቸዋል።
የህወሀት ጄነራሎችና ደህንነቶች ሽማግሌዎቹን በማስፈራራትና በማዋከብ ከአዲስ አበባ እንዲወጡ በማድረግ ላይ መሆናቸውንም መዘገባችን የሚታወስ ነው።