በድርቅ የተጠቁ 9.7 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን አሁንም በከፍተኛ ችግር ውስጥ ናቸው ተባለ

ኢሳት (መስከረም 2 ፥ 2009)

በኢትዮጵያ በስድስት ክሎች ተከስቶ ያለው የድርቅ አደጋ ከተላላፊ በሽታዎች ስርጭት ጋር ተዳምሮ በ9.7 ሚሊዮን ሰዎች ላይ አሉታዊ ተፅዕኖን እያደረሰ እንደሚገኝ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ገለጠ።

ካለፈው ዓመት ጀምሮ በሚሊዮን በሚቆጠሩ ሰዎች ላይ ጉዳትን እያደረሰ ያለው የድርቅ አደጋ ዕልባት አለማግኘቱን ያወሳው ድርጅቱ የኮሌራና ሌሎች ተላላፊ በሽታዎች ስርጭት ድርቁን በመከላከሉ ስራ ላይ እንቅፋት መፍጠሩን በጉዳዩ ዙሪያ ባወጣው ሪፖርት አመልክቷል።

ከ200 በላይ በሚሆኑ ወረዳዎች ውስጥ ጉዳትን እያደረሰ ያለው የድርቁ አደጋ እልባትን ያላገኘ ሲሆን፣ 9.7 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን አሁንም ድረስ ለምግብ ድጋፍ ተጋልጠው እንደሚገኙ ታውቋል።

ለተረጂዎች የሚያስፈልገው ድጋፍ ሙሉ ለሙሉ አለመገኘቱን ያስታወቀው ተመድ፣ በአገሪቱ ተከስቶ ያለው ድርቅ እስከቀጣዩ አመት ድረስ ቀጣይ ሊሆን እንደሚችልና የቅርብ ክትትልን እንደሚፈልግ አሳስቧል።

በኢትዮጵያ በግብርና ምርት በሚታወቁ አካባቢዎች ከቀጣዩ ወር ጀምሮ ይኖራል ተብሎ የሚጠበቀው ከፍተኛ የቅዝቃዜ የአየር ጸባይ በእርሻ ምርት ላይ ጉዳትን እንደሚያደርስ የአለም አቀፍ የሜትሮሎጂ ተቋም በመግለጽ ላይ ነው።

ሃገሪቱ ዳግም የሚያጋጥማት የሰብል ምርት መቀነስ ተጨማሪ ሰዎችን ለምግብ ተረጂነት ያጋልጣል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካልት ቅድመ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ የአለም የእርዳታ ድርጅቶች አሳስበዋል።

የአለም አቀፉ የምግብ ፕሮግራም (WFP) በበኩሉ በቀጣዮቹ ሶስት ወራት ብቻ 140 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልገው የገለጸ ሲሆን፣ ለአስቸኳይ ጊዜ የምግብ ተረጂዎች በአጠቃላይ ወደ 600 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ የገንዘብ ጉድለት ማጋጠሙን ለመረዳት ተችሏል።