ኢሳት (ሚያዚያ 7 ፥ 2008)
በኢትዮጵያ በድርቅ ከተጎዱ 10 ሚሊዮን በላይ ሰዎች መካከል 70 በመቶ የሚሆኑ በቀን አንድ ጊዜ ብቻ በመመገብ የእርዳታ አቅርቦትን እየተጠባበቁ እንደሚገኝ የአለም ምግብ ፕሮግራም (WFP) አርብ ይፋ አደረገ።
ከእነዚሁ ተረጂዎች መካከልም 80 በመቶ የሚሆኑት በአለም ጤና ድርጅት የተቀመጠን የእለት የምግብ ፍላጎት እያገኙ እንዳልሆነ ድርጅቱ ባወጣው ሪፖርት አመልክቷል።
በቀጣዮቹ ሰባት ወራቶች ተጨማሪ 425 ዶላር እንደሚፈልግ የገለጸው የአለም ምግብ ፕሮግራም አብዛኞቹ የአስቸኳይ ጊዜ የምግብ ፈላጊዎች ተገቢውን እርዳታ እያገኙ እንዳልሆነም አመልክቷል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ወደ ረሃብ ደረጃ ሊሸጋገሩ አንድ ደረጃ ብቻ የቀራቸው ወረዳዎች ከ 186 ወደ 219 ማደጋቸውን መግለጹም ይታወሳል።
ባለፉት ሶስት ወራቶች ከ10 ሚሊዮን ለሚበልጡ ተረጂዎች ሶስት ዙር ብቻ የምግብ እደላ እየተደረገ ሲሆን፣ የምግብ አቅርቦቱ እጅግ አነስተኛ መሆኑ ተገልጿል።
የእርዳታ ድርጅቶች ለተረጂዎች መድረስ ያለበት እርዳታ በወቅቱ ባለመቅረቡ ምክንያት ድርቁ እያደረሰ ያለው ጉዳት ከተጠበቀው በላይ እየሆነ መምጣቱን በመግለጽ ላይ ሲሆኑ ድርቁ ወደ ረሃብ ሊለወጥ ይችላል የሚል ስጋት መሆሩንም ይፋ አድርገዋል።
ለአስቸኳይ የምግብ እርዳታ ተጋልጠው ከሚገኙት መካከልም 15 በመቶ የሚሆኑት ህይወታቸውን ለመታደግ ሲሉ በራሳቸው መንገድ ምግብን ለማግኘት ጥረት እያደረጉ እንደሚገኝም የአለም ምግብ ፕሮግራም አክሎ ገልጿል።
የመንግስት ባለስልጣናት በበኩላቸው በጎረቤት ጅቡቲ በመጨናነቅ ምክንያት ወደ ሃገር ሊደርስ ያልቻለውን የእርዳታ እህል በመጓጓዝ ላይ መሆኑን አርብ አስታውቀዋል።
በየዕለቱም 17ሺ ሜትሪክ ቶን የእርዳታ እህል ወደሃገሪቱ እየገባ መሆኑን የብሄራዊ የአደጋ እና የስጋት ቅነሳ ኮሚሽን ኮሚሽነር የሆኑት አቶ ምትኩ ካሳ ለሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ተናግረዋል።
በወደብና በተሽከርካሪ እጥረት የተከሰቱ ችግሮች ተፈተዋል ያሉት ሃላፌው ሁሉም ተረጂዎች የሚያስፈልጋቸውን የምግብ መጠን እያገኙ ነው ሲሉም አክለው ገልጸዋል።