በድርቅ የተጎዱ ኢትዮጵያዊያን ሕይወት ለመታደግ በእንግሊዝ ያሉ ግብረሰናይ ድርጅቶች እርዳታ የማሰባሰብ ዘመቻ ጀመሩ

ሚያዚያ ፳፯(ሃያ ሰባት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በኢትዮጵያ በተከሰተው አሰቃቂ የረሃብ አደጋ የተጠቂዎችን ሕይወት ለመታደግ በእንግሊዝ ለንደን ከተማ ውስጥ የሚገኙ ለጋሽ ግብረሰናይ ድርጅቶች በጋራ በሆን እርዳታ የማሰባሰብ ዘመቻ ጀምረዋል።
ከ1977 ዓ.ም. ድርቅ በእጥፍ ሁኔታ የላቀ ሰብዓዊ ቀውስ ያስከትላል ተብሎ የተፈራው አሰቃቂው የዘንድሮ ርሃብ በሰዎችና በእንስሳት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ነው። ይፋ ሳይደረግ ከአንድ ዓመት በላይ በዘለቀው የኢትዮጵያ ርሃብ ቁጥራቸው ከ15 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎች በድርቁ የተጠቁ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ ከ10.2 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት ዜጎች አፋጣኝ የእለት የምግብ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል ሲል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታውቋል።
ይህንን ከግምት ውስጥ በማስገባት በእንግሊዝ ያሉ ለጋሾችና ሲቪክ ማኅበራት፣ ከእንግሊዝ የኢትዮጵያ ኮሚኒቲና ከዓለምአቀፍ ማኅበረሰብ ጋር በጥምረት በመሆን ድንኳኖችን በመትከልና ባነሮችን በመለጠፍ በሰር ቦብ ጊልዶፍ አማካኝነት በ1977 ዓ.ም. ተደርጎ እንደነበረው የእርዳታ ማሰባሰብና ማስተባበር ሥራዎችን እያከናወኑ ይገኛሉ።
ኢትዮጵያዊያን ዜጎች በአንድ ጥላ ስር በመሰባሰብ ችግረኞችን ለማገዝ የዘመቻው አንዱ አካል ሆነዋል። ከዘመቻው አስተባባሪዎቹ አንዱ የሆኑት አቶ ዮሃንስ መሰለ እንዳሉት ”እኛ እንደ ኢትዮጵያዊነታችን ለክስተቱ ምላሽ እንሰጣለን፤ በችግር ውስጥ ላለ ህዝብ ምላሽ መስጠት የዜግነት ግዴታችን ነው። ለዚህም ነው ወጣቶችና አዛውንቶች በጋራ በመሆን ገንዘባችንን፣ጊዜያችንንና እውቀታችንን በማስተባበር የእርዳታ ማሰባሰቡን የጀመርነው። በማለት ተናግረዋል:: እርዳታ ማሰባሰቡን ስራ ለማገዝ የቤተሰሰቦች ተሳትፎ፣ የሙዚቃ፣ ድራማ፣ የምግብ ዝግጅቶች፣ የስነ ግጥም ዝግጅቶች፣ ጨረታዎች ሲኖሩ ገቢውም ለኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበርና አፋጣኝ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው እንደሚውል ዘ ቮይስ ዘግቧል።