በድርቅ በተጎዱ አካባቢዎች የምግብ እጥረት ተከሰተ

ኢሳት (ሃምሌ 14 ፥ 2008)

በኢትዮጵያ በድርቅ በተጎዱ አካባቢዎች ወደ ረሃብ ሊሸጋገሩ አንድ ደረጃ ብቻ የቀራቸው ወረዳዎች ቁጥር 206 መሆኑንና በአለም አቀፍ የምግብ ፕሮግራም ሲሰራጭ የነበረው የምግብ አቅርቦት እጥረት ማጋጠሙን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ገለጸ።

ያጋጠመውን የምግብ አቅርቦት ለመቅረፍ 426 ሚሊዮን ዶላር በአስቸኳይ የሚያስፈልግ ሲሆን፣ በስደት ክልሎች ተከስቶ ያለው የድርቅ አደጋ አሁንም ድረስ ጉዳት እያደረሰ መሆኑን ድርጅቱ አስታውቋል።

የአለም አቀፍ ምግብ ፕሮግራም በተለያዩ አካባቢዎች ለአስችኳይ ጊዜ የምግብ እርዳታ ለተጋለጡ ሰዎች ድጋፍን ሲያደርግ ቢቆይም በተያዘው ወር የምግብ ስርጭቱ አቅርቦት ችግር እንዳጋጠመውና በተረጂዎች ላይ ጉዳይ ሊያጋጥም እንደሚችል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በወቅታዊ የሃገሪቱ የድርቅ አደጋ ዙሪያ ባወጣው ሪፖርት ሰስፍሯል።

መንግስት የድርቁ አደጋ እያደረሰ ያለውን ጉዳት ለመቅረፍ ውጤታማ ተግባራት ተከናውነዋል ቢልም አሁንም ድረስ ወደ ረሃብ ለመሸጋገር አንድ ደረጃ ብቻ የቀራቸው 206 ወረዳዎች መኖራቸው ታውቋል።

ለተረጂዎች የሚያስፈልገው ድጋፍ በወቅቱ ወደሃገሪቱ ባለመግባቱ ምክንያት ለከፋ የምግብ እጥረት የተጋለጡ ሰዎች እና ልዩ ክትትልን የሚሹ ወረዳዎች ቁጥር መቀነስን ሊያሳይ እንዳልቻለ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ካወጣው ሪፖርት ለመረዳት ተችሏል።

በቀጣዮቹ ስድስት ወራት ወደ ሃገሪቱ መግባት ያለበት አለም አቀፍ የምግብ አቅርቦት በወቅቱ የማይደርስ ከሆነም የምግብ ድጋፍን በመጠባባቅ ላይ ያሉ ሰዎች የከፋ የምግብ እጥረት ያጋጥማቸዋል ተብሎ ተሰግቷል።

አለም አቀፍ የህጻናት መርጃ ጥምረት ድርጅቶች በበኩላቸው በድርቁ መባባስ ምክንያት የከፋ የምግብ እጥረት ያጋጠማቸውና ልዩ እንክብካቤን የሚፈልጉ ህጻናት ቁጥር 2.3 ሚሊዮን አካባቢ መድረሱን ይፋ አድርገዋል።

ለአስቸኳይ የምግብ እጥረት ለተጋለጡ 10.2 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን መካከል ግማሽ ያህሉ ህጻናት ሲሆን፣ ከእነዚሁ መካከል ግማሽ ሚሊዮን የሚሆኑት የከፋ በሚባል የምግብ እጥረት ውስጥ መሆናቸው ታውቋል።

ከድርቁ ጎን ለጎን አዲስ አበባ ከተማን ጨምሮ በተለያዩ ክልሎች ከውሃ እጥረት ጋር የሚከሰቱ ተላላፊ በሽታዎች ተጨማሪ የድርቁ አደጋ እየሆኑ መምጣታቸውን የእርዳታ ተቋማት በመግለጽ ላይ ሲሆኑ፣ በመዲናይቱ አዲስ አበባ ከተማ ብቻ እስካሁን ድረስ ስድስት ሰዎች መሞታቸውን ለመረዳት ተችሏል።

የአለም ጤና ድርጅትና የኢትዮጵያ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የበሽታውን ስርጭት በቁጥጥር ስር ለማዋል ሃገር አቀፍ ዘመቻ እያካሄዱ መሆኑም ተገልጿል።