ኢሳት (ጥር 6 ፥ 2008)
በተያዘው አመት በኢትዮጵያ በተከሰተው የድርቅ አደጋ በአንድአንድ አካባቢዎች 90 በመቶ የሚሆን የእርሻ ሰብል መውደሙንና የዕህል ዋጋ ንረት አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን የለአም ምግብ ድርጅት ፕሮግራም (FAO) አርብ አስታወቀ።
በተለይ በምስራቅ የሃገሪቱ ክፍል በተከሰተው ድርቅ የእርሻ ሰብሎች ሙሉ በሙሉ መውደማቸውንና የድርቁ አደጋ ገጽታውን እየቀየረ መምጣቱን ድርጅቱ ገልጿል።
መቀመጫውን በጣሊያን ሮም ከተማ ያደረገው የዓለም ምግብ ፕሮግራም ሊያካሄድ ላሰበው እርዳታ 50 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልገው የገለጸ ሲሆን በቀጣዮቹ ጥቂት ወራቶችም የድርቁ ጉዳት እየከፋ እንደሚሄድ አስታውቀዋል።
በኢትዮጵያ የድርጅቱ ተወካይ የሆኑት አማዱ አላሃሪ ከምግብ እጥረቱ በተጨማሪ በበርካታ ቦታዎች የተከሰተው የውሃ እጥረት ችግሩን ውስብስብ አድርጎት ኣንደሚገኝ ለሮይተርስ ገልጸዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን ጨምሮ የአለም ግብረ ሰናይ ተቋማት በስድስት ክልሎች ተከስቶ ያለው የድርቅ አደጋ በተያዘው የፈረንጆች አመት እየተጠናከረ እንደሚሄድ በማሳሰብ ላይ ናቸው።
የአለም ምግብ ፕሮግራም በድርቁ ሳቢያ የእርሻና የቤት እንስሶቻቸው የሞቱባቸው አርሶ አደሮች ልዩ ድጋፍን በአስቸኳይ ካላገኙ በቀጣዩ የእርሻ ወቅት የእርሻ ስራቸውን ለማካሄድ እንደሚቸገሩም አመልክቷል።
በተያዘው የፈረንጆች አመት አስቸኳይ የምግብ እርዳታ የሚፈልጉ ሰዎች ቁጥር ወደ 15 ሚሊዮን ይደርሳል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን ወደ 7 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎችም በምግብ ራስን ማስቻል ፕሮግራም እርዳታን ያስገኛሉ ሲል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታውቋል።