ጥር ፱ ( ዘጠኝ )ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የኢህአዴግ መንግስትና ለጋሽ ድርጅቶች ዛሬ በአዲስ አበባ ይፋ ባደረጉት ሪፖርት በድርቅ ለተጎዱ 5 ሚሊዮን 600 ሺ ኢትዮጵያውያን ለአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ የሚሆን 948 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ወይም ከ20 ቢሊዮን ብር በላይ ገንዘብ ያስፈልጋል። አብዛኛው ገንዘብ በደቡብና ደቡብ ምስራቅ የአገሪቱ ክፍሎች ለሚገኙ ዜጎች የሚውል ነው።
ከዚህ ውስጥ የኢህአዴግ መንግስት 47 ሚሊዮን ዶላር ለመነሻ እንደሚለግስ አስታውቋል። ቀሪው ወጪ በአለማቀፍ እርዳታ ድርጅቶች ይሸፈን አይሸፈን አልታወቀም። አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ አምና ተከስቶ የነበረውን ድርቅ 75 በመቶ በራሳችን አቅም ተቋቁመነዋል በሚል መግለጫ መስጠታቸው ይታወቃል። ይሁን እንጅ አሁን በቀረበው እቅድ ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነው ወጪ እንዴት እንደሚሸፈን አልተገለጸም።
በሌላ በኩል በደቡብ ኦሞ ዞን በተከሰተው ድርቅ በታህሳስ ወር በሃመርና በናኩሌ ወረዳዎች ብቻ 6 ሺህ የቀንድ ከብት አልቀዋል። ይህን ተከትሎ የ2 ሚሊዮን ብር የመኖ ሣር ወደ ዞኑ ለማጓጓዝ ሙከራ እየተደረገ ቢሆንም፣ ውሃ በሌለበት ሁኔታ ሙከራው እንስሳቱን ከእልቂት እንደማይታደግ ከዞኑ ወደ ወረዳዎች የተንቀሳቀሰው የግብርና ባለሙያዎች ቡድን አሳውቋል፡፡
ከዚሁ ጋር በተያያዘ የደቡብ ኦሞና ሰሜን ኦሞ ድንበር/ወሰን የሆነውና ላለፉት 25 ዓመታት 5 ሺ 490 ሄክታር መሬት በመስኖ ሲያለማ የነበረው የ‹ወይጦ› ወንዝ በመድረቁ በወንዙ ዳርቻና ከወንዙ መስኖ የእንስሳት ፈጥኖ-ደራሽ ሳሮችን/መኖ ለማምረት የተጀመረው ሙከራም በወይጦ ወንዝ መድረቅ መቋረጡን ባለሙያዎች ጨምረው ገልጸዋል፡፡