በድሬዳዋ የጣለው ዝናብ በሰውና ንብረት ላይ ጉዳት አደረሰ

ኢሳት (ሚያዚያ 17 ፥ 2008)

ሰኞ ጠዋት በድሬዳዋ ከተማ የጣለ ከባድ ዝናብ ተከትሎ በተከሰተ የጎርፍ አደጋ በትንሹ አራት ሰዎች ሞቱ።

ለተከታታይ አምስት ሰዓታት ያህል የጣለው ይኸው ከባድ ዝናብ በከተማዋ በሚገኙ ሁለት ቀበሌዎች ላይ ከፍተኛ የንብረት ውድመት ማድረሱንና በጎርፍ የተወሰዱ ሰዎች ሊኖሩ እንደሚችልም ፖሊስ አስታውቋል።

በአካባቢው የጎርፍ አደጋን ለመከላከል ታስቦ የተሰራ ግድብም በጎርፍ አደጋው የተደረመሰ ሲሆን፣ የድሬ ዳዋ ከተማን ከሌሎች ቀበሌዎች የሚያገናኝ ድልድይም በጎርፉ አደጋ መወሰዱን ለመረዳት ተችሏል።

በድልድዩ ስር አሸዋ ሲጭኑ የነበሩ ሁለት ተሽከርካሪዎችም በጎርፍ የተወሰዱ ሲሆን፣ በተሽከርካሪው አካባቢ የነበሩ ሰዎች ህልውናም ሳይታወቅ መቅረቱን የከተማዋ አስተዳደር ገልጿል።

በድሬዳዋ ከተማ ከደረሰው የጎርፍ አደጋ በተጨማሪም ኤጀአነኒ በተባለች የገጠር ቀበሌም የመኖሪያ ቤቶች በጎርፍ መወሰዳቸውን ነዋሪዎች ለመገናኛ ብዙሃን አስረድተዋል።

በከተማዋ በደረሰው የጎርፍ አደጋ የሟቾች ቁጥር ሊጨምር ይችላል ተብሎ ስጋት መኖሩንም ከሃገር ቤት ከተገኘ መረጃ ለመረዳት ተችሏል።

የዛሬ አስር አመት በከተማዋ ደርሶ በነበረ ተመሳሳይ አደጋ ከ200 በላይ ሰዎች መሞታቸው ይታወሳል።

ባለፈው ወር በጅጅጋ ከተማ በደረሰ የጎርፍ አደጋ በትንሹ 28 ሰዎች ሞተው የነበረ ሲሆን፣ ከ50 የሚበልጡ ነዋሪዎችም በወቅቱ የገቡበት አለመታወቁ ተገልጾ እንደነበር መዘገቡ ይታወሳል።