በድሬዳዋ የታሰሩት እንዲፈቱ ተጠየቀ

(ኢሳት ዲሲ–ጥር 21/2011)በድሬዳዋ ባለፈው ሳምንት ከተካሄደው ህዝባዊ ተቃውሞ ጋር በተያያዘ የታሰሩት እንዲፈቱ ተጠየቀ።

በአንድ ሳምንቱ ተቃውሞ ከ500 በላይ ሰዎች በእስር ላይ እንደሚገኙ የአካባቢው ነዋሪዎች ገልጸዋል።

ፋይል

የታሰሩት ካልተፈቱ የስራ ማቆም አድማ ለማድረግ ነዋሪው በመዘጋጀት ላይ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።

ኢሳት ያነጋገራቸው የድሬዳዋ ከተማ ከንቲባ ህብረተሰቡን ያሳተፈ ሰላም የማስፈን እንቅስቃሴ ተጀምሯል ብለዋል።

የድሬዳዋ ውጥረት ሁለተኛ ሳምንቱን ይዟል። ምንም እንኳን እንዳለፈው ሳምንት ህዝቡ በአደባባይ ወጥቶ መንገዶችን በመዝጋት ተቃውሞ እያሰማ ባይሆንም ከተማዋ አሁንም ወደ መረጋጋት እንዳልመጣች ነው መረጃዎች የሚያመለክቱት።

ኢሳት ያነጋገራቸው ነዋሪዎች እንደሚሉት በአንዳንድ የከተማዋ ክፍሎች ግድያን ጨምሮ የተለያዩ ግጭቶች ቀጥለዋል።

የአንድ ሰው ሕይወት የጠፋበት ግጭት ተከስቷልም ይላሉ። መከላከያ ሰራዊት የከተማዋን ጸጥታ ሃላፊነት መረከቡ ከተገለጸ ካለፈው አርብ ወዲህ የጎዳና ላይ ተቃውሞ ቢቆምም ህዝቡ አሁንም ጥያቄዎቹ እንዲመለሱለት በተለያዩ የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች መቀጠሉን ያገኘነኛቸው መረጃዎች ያመልክታሉ።

ከነገ ጀምሮ ይደረጋል የተባለው የስራ ማቆም አድማ የዚህ እንቅስቃሴ አንዱ አካል መሆኑ ታውቋል።

ለነገ የታቀደው የስራ ማቆም አድማ በሰሞኑ ተቃውሞ የታፈሱና ወደ እስር ቤት የተወሰዱ ከ500 በላይ የከተማዋ ነዋሪዎች እንዲፈቱ ጫና ለመፍጠር እንደሆነ ተገልጿል።

የተገለጸ ሲሆን በከተማዋ በስፋት እየተካሄደ የሚገኘውን የጅምላ አፈሳ እንዲቆም ለመጠየቅም እንደሆነ ተመልክቷል።

የከተማዋ ከንቲባ አቶ ኢብራሂም ኡስማን ግን ሰላማዊ ሁኔታ ተፈጥሯል፣ ህብረተሰቡን ያሳተፉ የተለያዩ እንቅስቃሴዎች ይደረጋሉም ይላሉ።

ምንም እንኳን የከተማዋ ከንቲባ አቶ ኢብራሂም ኡስማን ሰላም እየተመለሰ ነው የሚል መግለጫ ቢሰጡም ከተማዋን አንቆ የያዛትን ስር የሰደደ ችግር ለመፍታት የሚያስችል ሁኔታ ባለመፈጠሩ ቀውሱ መቀጠሉ አይቀርም ሲሉ ነዋሪዎች ይናገራሉ።

በተለይም በከተማዋ 40 40 20 በሚል የተቀመረው አስተዳደራዊ መዋቅር ድሬዳዋ ላይ የተቀበረ ፈንጂ ሲሉ የሚገልጹት ነዋሪዎች የከተማዋ ከንቲባም በዚሁ ቀመር ወደ ስልጣን የመጡ በመሆናቸው የመፍትሄ አካል መሆን አይችሉም ይላሉ።

ነገ ይካሄዳል ስለተባለው የስራ ማቆም አድማ የከተማው አስተዳደር መረጃው እንደሌለው የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።

አሁን በደረሰን መረጃ በጅጅጋ ከቤተክርስቲያን ሲመለሱ የነበሩ አማኞች ላይ የድንጋይ ውርወራ መፈጸሙ ተሰምቷል።

ምዕመናኑ ከድንጋይ ውርወራው ሸሽተው መንግስት ይድረስልን የሚል ድምጽ ሲያሰሙ በጸጥታ ሃይሎች በተከፈተባቸው ተኩስ የሁለት ሰው ህይወት መጥፋቱ ታውቋል።