በድሬዳዋ ከጁምዓ ሰላት በሁዋላ የአቶ አብዲ ኢሌን አገዛዝ በመቃወም ህዝቡ ሰልፍ አደረገ

በድሬዳዋ ከጁምዓ ሰላት በሁዋላ የአቶ አብዲ ኢሌን አገዛዝ በመቃወም ህዝቡ ሰልፍ አደረገ
(ኢሳት ዜና ሚያዝያ 26 ቀን 2010 ዓ/ም)ላለፉት ሳምንታት በሽንሌ ዞን የአብዲ ኢሌ አገዛዝ በህዝቡ ላይ እየፈጸመ ያለውን ግድያ፣ አፈናና እስር በመቃወም የተጀመረው ተቃውሞ ዛሬም በድሬዳዋ ከተማ በተለያዩ መስኪዶች ሲካሄድ ውሎአል። ሙስሊሞች ከጁምዓ ሰላት በሁዋላ ፣ ነጻነት እንፈልጋለን የሚሉና ሌሎችንም መፈክሮች በወረቀት ላይ በመጻፍ ተቃውሞአቸውን አሰምተዋል።
የህዝቡን ጥያቄ ይዘው ወደ አዲስ አበባ ከተጓዙት ሽማግሌዎች መካከል አንዱ ለኢሳት እንደገለጹት ከጥያቄዎቻቸው መካከል አካባቢያቸውን ራሳቸው በመረጡዋቸው ሰዎች እንዲያስተዳድሩ እንዲደረግ፣ አብዲ ኢሌ እንደ ንጉስ ሆኖ የፈለገውን የሚያደርግበት ስርዓት እንዲያበቃ እና በክልሉ የሚገኙ በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ የሚሉት ይገኙበታል።
አብዲ ኢሌ የክልሉ ፕሬዚዳንት ብቻ ሳይሆን፣ የፓርቲው ሊቀመንበር፣ የፋይናንስ ክፍል ሃላፊ፣ የበጀት ሃላፊ በአጠቃላይ ብቸኛ ፈላጭ ቆራጭ ቆራጭ ንጉስ ነው የሚሉት የአገር ሽማግሌዎች፣ የፌደራል መንግስቱ መፍትሄ እንዲሰጣቸው ለመጠየቅ የክልሉን ምሁራንና የአገር ሽማግሌዎች በማካተት ወደ አዲስ አበባ መሄዳቸውን ተናግረዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ በአገዛዙ የተቋቋመው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን የሶማሊ ክልል ቅርንጫፍ ኮሚሽነር አቶ ጀማል መሃመድ ወረፋ ትናንት ከፍተኛ ድብደባ ተፈጽሞባቸዋል። አቶ ጀማል የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ አባል ሆነው በቅርቡ በፓርላማው ተሾመው ነበር።
ከሁለት ሳምንት በፊት አቶ ጀማል ወደ አዲስ አበባ እንደሄዱ ቤተሰቦች ታፍነው ከተወሰዱ በሁዋላ ማስፈራሪያ እንደረሰባቸው ኢሳት ዘግቦ ነበር። ኮሚሽነሩ ትናንት ወደ ጽ/ቤታቸው ሲያመሩ ጄ/ል አብዱልራህማንና ኮ/ል ሳናያሬ የተባሉ የክልሉ ከፍተኛ የደህነንት ሰዎች የአቶ ጀማልን መኪና በማስቆም ጠባቂዎቻቸውን መሳሪያ ካስፈቱ በሁዋላ ከፍተኛ ድብደባ ፈጽመውባቸዋል።
ኢሳት ለአቶ ጀማል በቀጥታ ስልክ በመደወል ለማነጋገር የሞከረ ሲሆን፣ አቶ ጀማል ህክምና ላይ መሆናቸውን በመግለጽ፣ ለጊዜው ምንም ተጨማሪ አስተያየት ለመስጠት ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ገልጸዋል።
በመንግስት የተቋቋመው የሰብአዊ መብት ድርጅት ባለስልጣን ሲደበደቡ፣ በዶ/ር አዲሱ ገ/እግዝአብሄር የሚመራው የሰብአዊ መበት ኮሚሽን እስካሁን መግለጫ አላወጣም።
የሶማሊ ክልል ጥምረት ለፍትህ ባወጣው መግለጫ፣ “ለኢትዮጵያው ጠ/ሚኒስትር ሱዳን ውስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን ማስፈታት በኦጋዴን እስር ቤት የሚገኙትን ከማስፈታት ቀላል ሆኖ ተገኝቶላቸዋል” ሲል ጠ/ሚንስትሩ እርሳቸውን በመደገፋቸው የታሰሩትን እንኳን ለማስፈታት አለመቻላቸውን ገልጸዋል።