(ኢሳት ዲሲ–ጥር 16/2011)በድሬዳዋ ከተማ በተቀሰቀሰ ተቃውሞ በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱ ተገለጸ።
በተቃውሞው የተገደለ ሰው ባይኖርም በርካታ ሰዎች በጥይት ተመተው መቁሰላቸውን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
ባለፈው ሰኞ ታቦት ወደ ቤተክርስቲያን በሚያመራበት ጊዜ በተወሰኑ አካላት ድንጋይ መወርወሩን ተከትሎ በቁጣ ለተቃውሞ የወጣው ህዝብ የተጠራቀመ ብስሶቱን በማሰማት ላይ እንደሆነም ተገልጿል።
ነዋሪውን ያገለለው የድሬዳዋ ከተማ መዋቅር እንዲፈርስ በህዝቡ ተጠይቋል።
ተቃውሞ ወደ አመጽ የተቀየረው የከተማው ከንቲባ ህዝቡን ለማነጋገር የጠሩትን ስብሰባ በመቅረታቸው እንደሆነም ኢሳት ያነጋገራቸው ነዋሪዎች ገልጸዋል።
በከተማዋ ባሉ ሁለት መንደሮች መንገዶች በተቃጠለ ጎማ ተዘግተው የተጠናከረ ተቃውሞ እየደረገባቸው ነው።
በተቃውሞው በእሳት የወደሙ መንግስታዊ ተቋማት መኖራቸውም ተመልክቷል።
መነሻው የአንድ ቀን አጋጣሚ ቢሆንም የተጠራቀመና ዓመታትን የዘለቀ የህዝብ ጥያቄና ብሶት አደባባይ የወጣበት ክስተት ሆኗል።
ባለፈው ሰኞ የጥምቀት በዓል ታቦት ለማስገባት የወጣው ህዝብ ላይ ካልታወቀ አቅጣጫ፣ ባልታወቁ ሰዎች ድንጋይ ውርወራ ይጀመራል።
ሁኔታው አለመረጋጋትን ቢፈጥርም በወቅቱ ታቦታቱን ወደ ማደሪያቸው የማስገባቱ ስነስርዓት በሰላም ተጠናቀቀ።
ይህ መነሻ የሆነው ተቃውሞ ባለፉት ሶስት ቀናት የድሬዳዋ ከተማን በቀውስ እንድትቆይ አድርጓታል።
ነዋሪው ወደ አመጽ ከመግባቱ በፊት የዓመታት ጥያቄዎቹን በሰላማዊ መንገድ በማቅረብ ላይ እንደነበረ ነው መረጃዎች የሚያመለክቱት።
ጥያቄዎቹ የከተማዋን ነዋሪዎች ባይተዋር ያደረገው፣ እንደሁለተኛ ዜጋ እንዲታይ ያስገደደው የከተማዋ አስተዳደር መዋቅር ላይ ያተኩሩ ናቸው።
ኢሳት ያነጋገራቸው ነዋሪዎች እንደሚሉት 40 40 20 በሚል የተዋቀረው የከተማዋ አስተዳደር የነዋሪውን መብት መሉ በሙሉ የገፈፈ ነው።
ሰላም ያጣንበት፣ የከተማው ወጣት በስደት ሀገር የለቀቀበት መዋቅር መፍረስ አለበት ወደ ሚል ተቃውሞ የተለወጠ ሲሆን መንገዶችን በድንጋይና በተቃጠሉ ጎማዎች በመዝጋት ዛሬን ጨምሮ ላለፉት ሶስት ቀናት ድሬዳዋ በተቃውሞ ላይ መሆኗን ነው ነዋሪዎች የሚገልጹት።
የተከማቸ ብሶት ፈንቅሎ የወጣበት አጋጣሚ ተፈጥሯል የሚሉት ነዋሪዎች መፍትሄ እንዲሰጠውም ጠይቀዋል።
በሰላም እየተካሄደ የነበረው ተቃውሞ ወደ አመጽ የተቀየረውም የድሬዳዋ ከተማ ከንቲባ ህዝቡን ለማነጋገር ከጠሩ በኋላ ከስብሰባው በመቅረታቸው እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል።
በከተማዋ አዲስ ከተማ በሚባል አካባቢ በርካታ ወጣቶች ከታጣቂዎች ጋር መጋጨታቸውን ቀስ እያለም ወደሌሎቹ የከተማዋ ክፍሎች መዛመቱን ነው የደረሰን መረጃ ያመለከተው።
ደቻቱ፣ ሳቢያን፣ ገንደ ቆሬና ዲፖ በተባሉ አካባቢዎች መንገዶች በተቃጠሉ ጎማዎችና በድንጋይ ተዘግተው ውለዋል።
በህዝብ ቁጣ የተቃጠሉ የቀበሌ ህንጻዎች እንዳሉም ተገልጿል።
በግጭቱ በጥይት የተመቱ ወጣቶች መኖራቸውን የገለጹት ነዋሪዎች በመንግስትና ህዝብ ንብረት ላይ ጥቃት እንዳይደርስ ህዝቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ጥሪ ቀርቧል።