በድሬዳዋ ሶስት የጦር ሄሊኮፕተሮች መውደማቸው ተገለጸ

ኢሳት (ሰኔ 9 ፥ 2008)

በቅርቡ በኢትዮ-ኤርትራ ድንበር የተካሄደውን ውጊያ ተከትሎ በዝግጅት ላይ በነበሩ ሄሊኮፕተሮች ላይ በደረሰ አደጋ፣ ሶስቱ ከጥቅም ውጭም መሆናቸውን የኢሳት የአየር ሃይል ምንጮች ገለጹ።

አደጋው የተከሰተው በድሬዳዋ አየር ምድብ ሲሆን፣ ለአደጋው መንስዔ ሆነ የተገኙት ሌ/ኮሎኔል ፀጋዘዓብ ካሳ የተባሉ አብራሪ መሆናቸውም ታውቋል።

ባለፈው ማክሰኞ ሰኔ 7 ቀን 2008 ዓም በኢትዮጵያ አየር ሃይል የድሬዳዋ ምድብ ውስጥ ሄሊኮፕተርን በመሬት ላይ የማሮጥ ስራ ወይንም ኢንጅን ቴስት ረንአፕ (Engine Test Runup) ሲያደርጉ የነበሩት ሌ/ኮሎኔል ፀጋዘዓብ ካሳ ሌሎች ሁለት የቆሙ ሄሊኮፕተሮችን በመግባታቸው ሶስቱም ሄሊኮፕተሮች ከጥቅም ውጭ ሆነዋል። አደጋውን ያደረሱት ሌ/ኮሎኔል ፀጋዓብ ካሳ የህወሃት ታጋይ እንደነበሩ ተመልክቷል።

በአደጋው ሶስቱ ሄሊኮፕተሮች ከጥቅም ውጭ ቢሆኑም በሰው ላይ የደረሰ ጉዳት አለመኖሩንም  መረትዳት ተችሏል።

በዚህም ሳቢያ የኢትዮጵያ አየር ሃይል ለግዳጅ ብቁ የሆኑት ሄሊኮፕተሮች ብዛት ከአራት እንደማይበልጥም የአየር ሃይል ምንጮች ያስረዳሉ።