ሐምሌ ፳፯ (ሃያ ሰባት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በአቶ አቡበክር አህመድ የክስ መዝገብ ስር የሚገኙ የድምጻችን ይሰማ የመፍትሄ አፈላላጊ አባላት ከ22 እስከ 7 አመታት በሚደርስ እስር እንዲቀጡ የፌደራሉ ከፍተኛው ፍርድ ቤት 4ኛ ወንጀል ችሎት ውሳኔ አስተላልፏል።
ጠበቃ ተማም አባቡልጉ ፍርዱን ፍርድ ነው ብለን ለመቀበል አስቸጋሪ ነው ብለውታል። ፍርድ ቤቱ አቶ አቡበክር አህመድ፣ አህመዲን ጀበል፣ ያሲን ኑሩ እና ከሚል ሸምሱ በ22 አመታት፣ በድሩ ሁሴን፣ ሳቢር ይርጉ፣ መሃመድ አባተ፣ አቡበክር አለሙ፣ እና ሙኒር ሁሴን በ18 አመታት ፣ ሼክ መከተ ሙሄ፣ አህመድ ሙስጠፋ፣ ሼክ ሰኢድ አሊ፣ ሙባረክ አደም እና ካሊድ ኢብራሂም በ15 አመታትና ሙራድ ሸኩር፣ ኑሩ ቱርኪ፣ ሼህ ባህሩ ኡመርና ጋዜጠኛ የሱፍ ጌታቸው በ7 አመታት ጽኑ እስር እንዲቀጡ ወስኗል።
ውሳኔውን በተመለከተ አስተያየታቸውን የተጠየቁት ጠበቃ ተማም አባቡልጉ ውሳኔውን ኢፍትሃዊ ነው ብለውታል። ጠበቃ ተማም ” ከመጀመሪያው ክሱ ወንጀል ሆኖ የሚያስከስስ አይደለም ” ያሉ ሲሆን፣ ክስ ቢሆን እንኳ የሽብር ሳይሆን ደንብ የመተላለፍ ክስ ሊሆን ይገባ እንደነበር ተናግረዋል።
“ስርአቱ የሚከሳቸው ሰዎች ተከራክረው ነጻ ሲወጡ አናይም፣ ሁሌም አሸናፊው አቃቢ ህግ ነው፣ ይሄ ስለፍትህ ስርአቱ ምን ይነግረናል?” ተብለው የተጠየቁት አቶ ተማም፣ ህግ ጠላት ብለህ የፈረጅከውን ሰው የምትመታበት አይደለም በማለት የመለሱት አቶ ተማም፣ “ኢትዮጵያ ትልቅ አገር ሆና እያለች እያነሰችብኝ ነው፤ እየጠፋ ያለው ፣ እየተዋረደ ያለው አገር ነው” በማለት ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል
ውሳኔውን በተመለከተ አስተያየቱዋን የጠየቅናት ሰሊም፣ ውሳኔው የሚጠበቅ መሆኑንና ትግሉን ለመቀጠል ትልቅ እድል ተከፍቷል ትላለች። ድምጻችን ይሰማ የሚለውን ተቀብሎ መታገል እንደሚገባ፣ በአጠቃላይ ስርአቱን ባለው መንገድ ሁሉ ታግሎ መቀየር እንደሚገባ ሰሊም አክላ ተናግራለች፡
ጀሚላ ሙሃመድ በበኩሉዋ በውሳኔው ብታዝንም፣ ከአምባገነን መንግስት ፍትህ እንደማትጠብቅ ተናግራለች። ውሳኔው የተላለፈው በኮሚቴ አባላቱ ላይ ብቻ ሳይሆን በመላው ሙስሊም ኢትዮጵያውያን ላይ ነው ብላለች
ሰኢድ ኢብራሂም በበኩሉ ውሳኔው እንደዜጋም እንደ ሙስሊምም በጣም አሳዛኝ እንደሆነበት ገልጿል። ኢህአዴግ ከገባ ጀምሮ ፍርዱ ተመሳሳይ መሆኑን የገለጸው ሰኢድ ውሳኔው ፖለቲካዊ ነው ፣ የተነበበውም የድራማ ጽሁፍ ነው ብሎታል ። ውሳኔው ለተጨማሪ ትግል ያነሳሳል ሲል ሰኢድ አክሏል