በዳንሻና ሰሮቃ የሚታየው ውጥረት እንደቀጠለ ነው

መጋቢት ፲፪ (አሥራ ሁለት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የወልቃይትን የአማራ ማንነት ጥያቄ ከሚመሩት መካከል አንዱ የሆኑት አቶ ሊለይ ብርሃነ በትግራይ ፖሊሶች ታፍነው መወሰዳቸውን ተከትሎ፣ የአካባቢው ህዝብ የጀመረው ተቃውሞ እንደቀጠለ ሲሆን፣ ተቃውሞውን ለመበተን በደንሻ ነዋሪዎች ላይ ጥይቶችን ተኩሰዋል። የፖሊስ እርምጃ ያበሳጫቸው ነዋሪዎች መንግዶችን በመዝጋት የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲቋረጥ ያደረጉ ሲሆን፣ በአካባቢው ያለው ውጥረት ይህን ዜና እሳካጠናከርንበት ጊዜ ድረስ ቀጥሎአል።
የትግራይ ልዩ ሃይለ ፖሊስ አባላት የወልቃይትን የአማራ ማንነት ጥያቄ ይመራሉ የሚሉዋቸውን ሰዎች ሲያስፋራሩ ቆይተዋል። አቶ ሊለይ አቋማቸውን በአደባባይ በድፍረት በመግለጽ የሚታወቁ ሲሆን፣የህወሃት አስተዳደር፣ቀድም ብሎ ሲልከው የነበረውን ማስፈራሪያ ትኩረት ባለመስጠት አዲስ አበባ ድረስ በመሄድ ለመንግስት ጥያቄ ያቀረቡ ናቸው።
ግጭቱ እንደተነሳ የስልክ መስመር እንዲቋረጥ መደረጉን የአካባቢው ሰዎች ለኢሳት ተናግረዋል። የኮሚቴው አባላት የትግራይ መስተዳደር እየወሰደ ያለው እርምጃ ችግሩን የሚያባብሰው ነው በማለት እያሰጠነቀቁ ነው።