በዲላ ዩኒቨርስቲ ግጭቱ ተባብሶ ሊቀጥል እንደሚችል ተማሪዎች ስጋታቸውን ገለጹ

ታኀሳስ ፳፭ (ሃያ አምስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ከሶስት ቀናት በፊት በዲላ ዩኒቨርስቲ ምሽት ላይ በተመሳሳይ ሰአት በፈነዱ 4 ቦንቦች አንድ ተማሪ ወዲያውኑ ሲሞት፣ አንደኛው ሆስታል ከገባ በሁዋላ መሞቱ መዘገቡ ይታወሳል። ፍንዳታውን ተከትሎ 10 ተማሪዎች በጩቤ የተወጉ ሲሆን፣ አንዳንድ ተማሪዎች ለዘጋቢያችን እንደገለጹት ጉዳቱን ያደረሱት የዩኒቨርስቲው ማህበረሰብ አባላት አለመሆናቸውን ተናግረዋል። በፍንዳታው አንድ አዳማና ሌላ ደብረብርሃን ልጅ ሲገደሉ፣ አንድ አርባ ምንጭ ልጅ ደግሞ እግሩ ተቆርጧል። ይህን ተከትሎ ተማሪዎች ግቢውን ለቀው ሲወጡ፣ የፌደራል ፖሊስ ወደ ግቢው እንዲገቡ ያስገደዳቸው ሲሆን፣ እንደገና 3 ተማሪዎች መጸዳጃ ቤት ውስጥ ታርደው ተጥለው ተገኝቷል።
ዘጋቢያችን እንደገለጸው ሟቾቹ ለገዳራ በሚባለው ወንዝ አካባቢ ተጥለው የተገኙ ሲሆን፣ ገዳዮቹ በዚሁ በኩል ገብተው ጥቃቱን እንደፈጸሙት ገልጿል። በርካታ ተማሪዎች የተዘረፉ ሲሆን፣ በርካታ ሴት ተማሪዎች ደግሞ ተደፍረዋል።
ትናንት ደግሞ በግቢው ውስጥ እሳት የተነሳ ሲሆን፣ ድርጊቱ ከመፈጸሙ በፊት ወሬው በከተማው አስቀድሞ ይሰራጭ ነበር ብሎአል። ተማሪዎች ከከተማው ለመውጣት ሙከራ ቢያደርጉም አልተሳካላቸውም። ተማሪዎችን ጭነው ሲወጡ የተገኙ 10 ሚኒባሶች ተይዘዋል። ተማሪዎች ከፍተኛ ችግር ላይ መውደቃቸውን እየገለጹ ሲሆን አንዳንዶች በእግራቸው እየጠፉ ወደ አዋሳና አዋሳኝ ከተሞች ጉዞ ጀምረዋል።
ዘጋቢያችን አንዳንድ ነዋሪዎችን አነጋግሮ እንደገለጸው የጥቃቱ መንስኤ በቅርቡ ከስልጣን ከወረዱት ከደ/ር ስለሺ ቆሬ ጋር የተያያዘ ነው። ዶ/ር ስለሺ በከፍተኛ ሙስና ወንጀል ተከሰው ከስልጣን እንዲወርዱ መደረጉን ኢሳት መዘገቡ የሚታወስ ሲሆን፣ ይህን ተከትሎ የብሄረሰቡ ተወላጆች ዲኑ ወደቦታው እንዲመለስ መጠየቃቸውንና ጥያቄያቸው መልስ ባለማግኘቱ እርምጃው ተወስዷል።
በሌላ በኩል ደግሞ በኦሮምያ ከተጀመረው ህዝባዊ ተቃውሞ ጋር በተያያዘ ሰላማዊው ተቃውሞ ሌላ መልክ እንዲይዝ ለማድረግ ሆን ተብሎ በገዢው ፓርቲ ካድሬዎች የተቀናባበረ ፍንዳታ ነው የሚሉ አስተያየቶችም እየተሰጡ ነው።
ዲላ ሁለተኛ እና አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ዛሬ በፖሊሶች በከፍተኛ ሁኔታ ሲጠበቁ ውለዋል፣ ተማሪዎችም ትምህርት አቋርጠዋል። የዲላ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ደግሞ ገንዘብ ከባንክ ለማውጣት ሲሯሯጡ ውለዋል። በርካታ ተማሪዎች በቤተክርስቲያንና በመስጊዶች እያደሩ መሆኑም ታውቋል።