በዲላ አንድ የመንግስት ሹም አንድ ወጣት ገድለ የወጣቱን አባትም አቆሰለ

ታህሳስ  ፳፮(ሃያ ስድስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በጌዲዮ ዞን በዲላ ከተማ ኮማንደር ግርማ በየነ የተባለ የዞኑ የፖሊስ የሰው ሀብት ማደራጃ መምሪያ ሃላፊ ድርጊቱን የፈጸመው አባትና ልጅ ከግቢያቸው ፊት ለፊት ቆመው የግል ጉዳያቸውን በሚነጋገሩበት ጊዜ ነው። ከምሽቱ 12 ሰአት አካባቢ ኮማንደሩ ወደ ቤቱ እየሄደ በነበረበት ሰአት አባት እና ልጁን ውጭ ላይ ቆመው ሲያገኛቸው፣ ምን ታደርጋላችሁ ብሎ መጠየቁን፣ የሟቹ አባትም ” ከልጄ ጋር የግል ጉዳያችንን እየተወያየን ነው” ብለው መመለሳቸውን፣ ወጣቱም ” ምንም ችግር እንደሌለ ማስረዳቱን” ቤተሰቦች ተናግረዋል፡፡  ይሁን እንጅ  ኮማንደሩ ሽጉጥ በማውጣት የ14 አመቱን ታዳጊ ወጣት ከገደለው በሁዋላ አባትየው “ልጄን ገድለህ የት ትሄዳለህ?’ ብለው ሲጠይቁት  እሳቸውንም በሁለት ጥይት እንደመታቸው ታውቋል። ወጣቱ ወዲያውኑ ሲሞት አባትየው ደግሞ በጽኑ ቆስለው ወደ አዋሳ ሪፈራል ሆስፒታል ተወስደዋል።

የከተማው ህዝብ በተለይም ተማሪዎች በትናንትናው እለት ከፍተኛ የተቃውሞ ሰልፍ ያደረጉ ሲሆን፣ ወጣቱ ትናንት መቀበር ቢኖርበትም ህዝቡ የፖሊስ ማስረጃ ሳይሰጥ እና ገዳዩ በቁጥጥር ስር ሳይውል አይቀበርም የሚል አቋም በመያዙ ወጣቱ ዛሬ ሊቀበር ችሎአል:፡ ፖሊስ ለሟች ቤተሰቦች አስፈላጊውን ማስረጃ የሰጠ ሲሆን፣ በዛሬው እለትም ረብሻ ይነሳል በሚል ቁጥጥር ሲያደርግ አርፍዷል።

አንድ ከፍተኛ የፖሊስ ባለስልጣን ለኢሳት እንደገለጹት ኮማንደሩ በቁጥጥር ስር የዋለ ሲሆን፣ ገዳዩም እና ሟቹም ሆነ የሟቹ አባት ከዚህ ቀደም እንደማይተዋወቁ ገልጸዋል።

አንድ የሟቹ የቅርብ ዘመድ እንደገለጸው ሟቹና አባቱ የሌላ አካባቢ ተወላጅ በመሆናቸው የተወሰደ እርምጃ ነው። እንዲህ አይነት እርምጃዎች ሲወሰዱ የሚጠይቅ አለመኖሩንም ተናግሯል።