በዱባይ ኢትዮጵያውያን ደማቅ ድል አስመዘገቡ

ኢሳት (ጥር 12: 2009)

በዱባይ ማራቶን ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ተከታትለው በመግባት ደማቅ ድል አስመዘገቡ። የኢትዮጵያውያኑ ታምራ ቶላ እና ወርቅነሽ ደገፉ በዱባይ ማራቶችን አንደኛ በመሆን ማሸነፋቸው አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

ሁለቱም ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ውድድሩን በአንደኝነት በማሸነፋቸው እያንዳንዳቸው የአንድ መቶ ሺህ ዶላር ሽልማት ማግኘታቸውን ዘገባዎች አመልክተዋል።

በወንዶች በተደረገው ውድድር በ5ኛ ደረጃ መሃል ላይ ከገባው አንድ የኬንያ ሯጭ በስተቀር ከ1ኛ እስከ 10 ተከታትለው በመግባት በዱባይ ማራቶን አለምን አስደንቀዋል። በሴቶች ማራቶንም ከ1ኛ እስከ 9ኛ ተከታትለው በመግባት ኢትዮጵያውያኑ በሩጫ ውድድር አይበገሬነታቸውን አሳይተዋል።

ታምራት ቶላ በወንዶች ማራቶን 2:04 ደቂቃ 10 ሰከንድ በመጨረስ በአንደኝነት አሸንፏል። ወርቅነሽ ደገፉ ደግሞ በሴቶች ማራቶን 2 ሰዓት 22 ደቂቃ 35 ሴኮንድ በመጨረስ አንደኛ ወጥታለች።

ታምራት ቶላ በዱባይ ማራቶን ውድድር ከዚህ ቀደም የነበረውን ክብረወሰን በማሻሻሉ ተጨማሪ 50ሺ ዶላር ማግኘቱንም ለማወቅ ተችሏል።

በውድድሩ አትሌት ቀነኒሳ በቀለ መሃል ላይ አቋርጦ መውጣቱን ከስፍራው ተዘግቧል።

በዱባይ በተካሄደው የሩጫ ወድድር የ10 እና 4 ኪሎሜትሮችን ጨምሮ በጠቅላላው 33ሺህ አትሌቶች መሳተፋቸውን የኤሜሬትስ ዜና አገልግሎት ዘገባ ያመለክታል።