በደጋን ወረዳ ከ100 በላይ ሰዎች ታሰሩ አካባቢው በፌደራል ፖሊስ ተከቧል

ጥቅምት ፳፮ (ሀያ ስድስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በደቡብ ወሎ ዞን በደጋን ወረዳ ከሳምንታት በፊት የተፈጠረውን ችግር ተከትሎ አካባቢው ከትናንትጀምሮ እንደገና በፌደራል ፖሊስ ቁጥጥር ስር ከዋለ በሁዋላ ከ100 በላይ ሰዎች ተይዘው መታሰራቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ገልጠዋል።

ወጣቶችም አካባቢውን ለቀው ወደ ወደ ገጠር በብዛት መሰሰደዳቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል።

ከታሰሩት መካከል በከተማዋ ውስጥ በእድሜ አዛውንት የሆኑት የ90 አመቱ አቶ እንድሪስ ከማል ይገኙበታል።

ኢሳት አንዳንድ ወጣቶችን ለማናገር የቻለ ሲሆን፣ ወጣቶቹ እንደሚሉት አካባቢው በሙሉ በፌደራል ፖሊስ በመከበቡ ወደ ጎረቤት አገሮች ወይም ወደ ሌሎች የኢትዮጵያ ከተሞች ለመሸሽ አልቻሉም።

 

እስረኞቹን ሆስፒታል ውስጥ በማጠራቀም ወደ ተለያዩ ቦታዎች ወስደው  እያሰሩዋቸው መሆኑ ታውቋል።

ባለፈው ወር በደጋን በተነሳው ግጭት ከ4 ሰዎች ያላነሱ ሰዎች መገደላቸው ይታወሳል። የግጭቱ መንስኤ በአዲስ አበባ ከሚካሄደው የሙስሊሞች ተቃውሞ ጋር የተያያዘ ነው።

በሌላ ዜና ደግሞ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት መቋቋሙን የመንግስት የመገናኛ ብዙሀን ይፋ አድርገዋል።

ሼክ ኪያር መሃመድ አማን የምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት፣ ሼክ ከድር መሃመድ፣  ምክትል ፕሬዝዳንት

አቶ መሃመድ አሊ ደግሞ ጸሃፊ ሆነው ተመርጠዋል።

አወዛጋቢ የሆነው የሙስሊሞች ጥያቄ በውል ባልተቋጨበት በዚህ ጊዜ አዲስ የእሰልምና ምክር ቤት ምርጫ መደረጉ ውዝግቡ እንዲቀጥል የሚያደርገው መሆኑን ታዛቢዎች ይናገራሉ።

በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች ሙስሊሞች ከሚያነሱዋቸው ጥያቄዎች መካከል አንዱ የሀይማኖት መሪዎቻችንን ያለመንግስት ታልቃ ገብነት በዲሞክራሲያዊ መንገድ እንምረጥ የሚል ነው።