በደንቢያ የቴክኒክ እና ሙያ ኮሌጅ መምህራን አድማ እንደቀጠለ ነው

ግንቦት ፰(ሥምንት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በደንቢያ ወረዳ በቆላድባ ከተማ የሚገኘው የቴክኒክ እና ሙያ ኮሌጅ መምህራን ባለፈው አርብ የጀመሩትን አድማ በመቀጠላቸው ተማሪዎች ወደ ቤታቸው መመለሳቸው ታውቋል። የወረዳው ባለስልጣናት አድማውን ከሚያደርጉ መምህራን ጋር ለመነጋገር ያደረጉት ሙከራ ፣ መምህራኑ ባሳዩት ጠንካራ አቋም ምክንያት አልተሳካም።
የአድማው መነሻ ኮሌጁን ሲያስተዳድሩ የነበሩት መምህር ሙሉ አበበ እና ምክትላቸው ሰይድ ካሴ ከሃላፊነታቸው በመነሳታቸው ነው። መምህራኑ “የመብት ጥያቄ አንስተናል ጥያቄያችን ካልተመለሰ ስራ አንጀምርም” የሚል ጠንካራ አቋም የያዙ ሲሆን፣ ተማሪዎችም ለመምህራን ድጋፋቸውን እየሰጡ ነው።